የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፉ ታገደ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2011) የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፍትሐብሄር ችሎት በቅርቡ እጣ የወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለእድለኞች እንዳይተላለፉ አገደ፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቱን ለማግኘት ተመዝግበው 100 በመቶ የከፈሉ 98 ዜጎች ክስ መመስረታቸውን ተከትሎ የፍርድ ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፉ በችሎቱ ታግደዋል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የቤቶቹን ዋጋ መቶ በመቶ በመክፈል ቅድሚያ ለማግኘት የገባነው ውል አለ ያሉ 98 ተመዝጋቢዎች ናቸው ክስ የመሰረቱት።

ተመዝጋቢዎቹም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከሰዋል።

በመመሪያው መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕጣ አውጥቶ ለእድለኞች ማከፋፈል ሲገባው የከተማ አስተዳደሩ መመሪያን በመጣስ 100 በመቶ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች እያሉ ከ40 በመቶ ጀምሮ የቆጠቡትን በእጣው በማካተት ዕጣውን አውጥቷል። ይሕም  አሰራር ከሕግና ከውል ውጪ ነው በሚል የቤቶቹ እጣ አወጣጥ ትክክል አለመሆኑን  በክሳቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም አሁን የተጀመረው የፍርድ ሂደት እስኪቋጭ ድረስ የቤቶቹን ካርታ ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፍ አግዷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተከሳሽ ተቋማትን ምላሽ ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 29/ 2011 ዓመተ ምህረት ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ሰኔ 10 ክርክር ለመጀመርም ቀጠሮ መስጠቱ ነው የተነገረው።

ባለፈው የካቲት 27 /2011 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ18 ሺህ በሚበልጡ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ እጣ ማውጣቱ ይታወሳል።