የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን ኤርትራ ለመሄድ ጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 3/2010) የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን ከአስመራ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ጠየቀ።

ለኤርትራ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተላከ ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱ ከተሞች የእግር ኳስ ክለቦች መሀል በአስመራ የወዳጅነት ግጥሚያ ለማደረግ ተፈልጓል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ በከተማው ከንቲባ በአቶ ተቀባ ተባባል ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ ጥያቄው መቅረቡ ታውቋል።

ጎንደር ከተማና ኤርትራ በባህል በጋብቻና በኢኮኖሚ የተሳሰረ ታሪክ ያላቸው መሆናችውን የሚያትተው ደብዳቤው በስፖርቱ ቀደም ሲል የነበረው ወንድማማችነት፥ ፍቅርና መተሳሰብ በወጣቱ ዘንድ በልዩ ስሜት የሚታወስ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ይህን ወንድማማችነት ለመቀጠል በኤርትራ ከሚገኝ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ከሚገኝ የእግር ኳስ ክለብ ጋር የፋሲል ከነማ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ እንፈልጋለን ይላል በደብዳቤ የተላለፈው መልዕክት።

የፋሲል ከነማ የስፖርት ክለብ አስመራ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ እንዲፈቀድ የግብዣ ጥያቄ መቅረቡ የተገለጸ ሲሆን ከኤርትራ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል