የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ መቱ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2011) መንግስት ጥያቄአችንን ለመመለስ ዝግጁ አይደለም በሚል የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ከዛሬ የጀመረ የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ተገለጸ።

ፋይል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር አድማውን ህገወጥ ሲሉ ገልጸውታል።

የድህረ ምረቃ ተማሪዎቹ እስከነገ ወደ ስራቸው የማይመለሱ ከሆነ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አስተዳደር ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል።

የስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ግን ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ከድንገተኛ የህክምና አገልግሎቶች ውጪ ያሉትን ስራዎች በማቆም ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በድህረ ምረቃ ተማሪዎች እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት ስራ ማቆም ተገቢ አይደለም ሲሉ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።