የጎዛምን ሆቴል ባለቤት ለሕዝብና ለሃገር እጨነቃለሁ አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 6/2010) በደብረማርቆስ አቶ በረከት ስምኦን ታይተዋል በሚል ጉዳት የደረሰበት የጎዛምን ሆቴል ባለቤት ከንብረታቸው ይልቅ ለሕዝብና ለሃገር እንደሚጨነቁ ገለጹ።

የሆቴሉ ባለቤት ዶክተር ምንውየለት ሞሴ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ሆቴሉን በትውልድ አካባቢውያቸው የገነቡት ሕዝቡ እንዲጠቀምና ሀገርን ለማሳደግ ነው።

ከ40 አመታት በላይ በውጭ ሀገር የኖሩትና በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ላይ የቆዩት ዶክተር ምንውየለት ሞሴ ሕዝቡ በኢትዮጵያ ፍትህ እስኪሰፍንና እኩልነት እስኪረጋገጥ ድረስ ትግሉን መቀጠል አለበት ብለዋል።

ለዶክተር አብይ አህመድ የሚሰጠው ድጋፍም መቀጠል እንደሚኖርበትም ነው የገለጹት።

በጎዛምን ሆቴል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስም ኣአሁንም የምጨነቀው ለሃገሬና ለወገኔ በጠቅላላው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ሲሉም ዶክተር ምንውየለት ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በደብረማርቆስ ከተማ አቶ በረከት ስምኦን ታይተዋል በሚል የጎዛምን ሆቴልን ጨምሮ ተሽከርካሪዎችና የሆቴሉ ንብረቶች ወድመዋል።ትልቅ ሰው የተባለው ሆቴልም ከቀደመው አገዛዝ ጋር ባለቤቷ የጥቅም ትስስር አላቸው በሚል ጉዳት መድረሱን መዘገባችን ይታወሳል።