የግብፅ መንግስት የአባይ ወንዝን አጠቃቀም በተመለከተ በዩጋንዳ ምክክር እንዲካሄድ ጥያቄ አቀረበ

ኢሳት (ግንቦት 7 ፥ 2009)

የግብፅ መንግስት በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ከሰባት አመት በፊት አቅርቦ የነበረው ሃሳብ በዩጋንዳ ዳግም ምክክር እንዲካሄደበት ጥያቄን አቀረበ።

ግብፅ ያቀረበችውን ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎ የዩጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በናይል ምክር ቤት አባላት ዘንድ በፕሬዚደንቶች ደረጃ በቀጣዩ ሳምንት ምክክር እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል። ይሁንና ኢትዮጵያ በግብፅ የቀረበውን ሃሳብ በአግባቡ ለመመልከት ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት የውይይቱ ቀን እንዲፈጸም ጥያቄ ማቅረቧን Daily News Egypt የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል። 

የዩጋንዳ መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው ግብፅ ባቀረበችው ሃሳብ ላይ ሊካሄድ የታሰበው የውይይት መድረክ በሰኔ ወር አጋማሽ እንዲካሄድ መወሰኑን አስነብበዋል።

ግብፅና ሱዳን ያላጸደቁት ስምምነት በአባይ ተፋሰስ ሃገራት መካከል በዩጋንዳ ኢንተቤ ከተማ እንደፈረጆቹ አቆጣጠር 2010 መፈረሙ ይታወሳል። የዚሁኑ አዲስ ስምምነት መድረስ ተከትሎ ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ እንዲካሄድ አቅርባ የነበረው ሃሳብ ውይይት ሳይካሄድ መቅረቱን ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ ስጋት ያደረባት ግብፅ ሃሳቧ በድጋሚ ለውይይት እንዲቀርብ ማግባባት እያካሄደች መሆኑ ታውቋል።

ሃገሪቱ በወንዙ ፍሰት ላይ እንዲካሄድ ያቀረበችው ሃሳብ በወንዙ ዙሪያ የሚካሄዱ ፕሮጄክቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጠውና ስምምነት እንዲደረስበት የምትፈልግ መሆኑም ተመልክቷል።

ግብፅ ከኢንተቤው ስምምነት ራሷን ብታገልም ጥቅሟን ለማስጠበቅ ስትል ሃሳቧ በተፋሰሱ ሃገራት ዘንድ ምክክር እንዲካሄደበት ጥረት እያደረገች መሆኑ ይነገራ።

ኢትዮጵያ ከስድስት አመት በፊት የአባይ ግድብን ለመገንባት መወሰኗን ተከትሎ ከግብፅ ጋር ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት መቆየቷ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ያቋቋሙት የባለሙያዎች ቡድን የግድቡ ግንባታ በታችኛው ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ በማጥናት ላይ ሲሆኑ፣ የባለሙያዎቹ ቡድን የሚሰጡት ውሳኔ ይግባኝ የሌለው እንደሆኑ በተደረሰው ስምምነት ሰፍሯል።

በሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች እየተካሄደ ያለው ይኸው ጥናት ከአምስት ወር በኋላ ለሶስቱ ሃገራት መንግስታት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ጥናቱን ለማካሄድ ወደ አምስት ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ለቡድኑ ወጭ ማድረጋቸውም ታውቋል።

የአባይ ግድብ ግንባታ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ የለም በማለት ኢትዮጵያ ምላሽን ስትሰጥ ቆይታለች።