የጌዲዮ ተፈናቃዮች ሰቆቃ እየከፋ መምጣቱ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 2/2011)ከጌዲዮ የተፈናቀሉ ዜጎች ሞትና ሰቆቃ እየከፋ መምጣቱን ተፈናቃዮቹ ገለጹ።

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት በየቀኑ 4ና 5 የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸው እያለፈ ነው።

ከችግሩ አስከፊነት የተነሳ የሞቱትን ሰዎች የመቅበር አቅም ስለሌለ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ነው አስከሬኖቹን እየሰበሰበ የሚቀብረው ብለዋል ተፈናቃዮቹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የኦሮሚያ ፕሬዝዳንትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተፈናቃዮቹን ጎብኝተው በ6 ወር ውስጥ ድጋፍ ይደረጋል ቢሉም የተባለውን ድጋፍ ግን ማየት አለመቻላቸውን ነው የገለጹት።

የጉጂ ኦሮሞዎች በጌዲዮ ተወላጆች የከፋ የሚባል ጥቃት የጀመሩት በመጋቢት 18/2010 ነበር ያላሉ።

በወቅቱም የተፈጠረው ችግር በአንድ ጊዜ አምስት ቀበሌዎችን ያዳረሰና ከ60ሺ በላይ ነዋሪዎችን ከቀያቸው ያፈናቀለ ነው

እነዚህ ተፈናቃዮች በወቅቱም ለችግሩ መፍትሄ ሰጥቻለሁ በሚል አካል ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር ይላሉ።ነገር ግን መኖያቸው ወድሞ ስለነበር መግቢያ አላገኙም ይላሉ ተፈናቃዮቹ።

ወደ ቦታቸው ሲመለሱም ለችግራቸው ጆሮ ሰጥቶ ያዳመጣቸውም ሆነ ይህንን ችግር ያደረሱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የተደረገ ነገር የለም።

የነዚህ ተፈናቃዮች ችግር ባልተፈታበትና ማረፊያና በቂ የሚባል ድጋፍ ባለገኙበት ሁኔታ ውስጥ ሌላ ጥቃት መፈጸሙንና በርካቶችን ለከፋ ችግር መዳረጉን ነው የሚናገሩት።

ነዋሪዎቹ በትንሹ ከአንድ ሚሊየን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በሁለት መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ከ45ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በመሞትና በመኖር መካከል ያሉ ናቸው።

በቀን በትንሹ ከ5 እስከ 10 ሰዎች ይሞታሉ።የሞቱትንም የሚቀብራቸው ስለሌለና መዘጋጃ ቤቱ እንዲቀብራቸው ለማድረግ መናሃሪ ያ ውስጥ እንደሚጣሉ ነው የሚናገሩት።

በጌዲዮዎች ላይ የዘር ማጥፋት ስራ ተሰርቷል ሲሉ የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ ከ4 መቶ በላይ የሚሆኑ የጌዲዮ ተወላጆች ጌዲዮ በመሆናቸው ብቻ እየታረዱ ገደል ውስጥ እንዲጣሉ መደረጉን በሃዘን ይናገራሉ።–ማንም የሚደርስላቸውና ተቆርቋሪ የሚባል አካልም እንደሌላቸው ነው የገለጹት።

ይህን ሁሉ መከራ ያሳለፈው የጌድዮ ህዝብ ከቀዬው ተፈናቅሎ ለከፋ ችግር ከተጋለጠ አንድ አመት ሊሞላው ነው ይላሉ።

በአሁን ሰአት ተፈናቃዮቹ በቀን አንድ ዳቦ እየተሰጣቸው ያለምንም ህክምናና ያለምንም እርዳታ በስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ አሁንም አስቸኳይ እርዳታ የማያገኙ ከሆነ አደጋው ከዚህም በላይ ሊከፋ እንደሚችል ነው የተነገሩት ።