የደቡብ ኦሞ መምህራን ያነሱዋቸው አገራዊ ጥያቄዎች ባለስልጣናቱን አስቆጡ

ሚያዚያ ፲፰(አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሚያዚያ 10 ቀን 2008 ዓም የጸረ ሙስና ጥምረት በሚል ፣ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ቦዲ ፣ የ8 ወረዳዎች ጸረ-ሙስና ኮሚሺነሮች፣ የሃይማሮት ተቋማት ተወካዮች፣ የእድር አመራሮች፣ የመምህራን ማህበራት፣ የንግድ ማህበረሰብ ማህበር ተወካዮች፣ የሴቶችና ወጣቶች ፎረም እንዲሁም የደኢህዴን ተወካዮች በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ መምህራንና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች በርካታ አገራዊ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ተወካይ “ ስለሙስና ብናወራም ሙስና እየተስፋፋ፣ እየፋፋና ስር እየሰደደ ሲሄድ እንጂ ሲጠፋና ሲቀንስ አላየንም” ያሉ ሲሆን፣ ጥቆማ በሚያቀርቡና በግልጽ በአደባባይ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም በዜጎች ላይ የሚደርሰውን በደል በሚዲያ የሚያጋልጡ፣ስለህዝብ ሃብት በተለይም በቅርብ ጊዜ በዞናችን ስለተፈጸመው የመሬት ቅርምት ያጋለጡ፣ በማኅበረሰቡ አንቱታ የተቸራቸው እነ ዓለማዬሁ መኮንን እና እነ ስለሺ ጌታቸው ታስረው በሌሊት አዋሳ ተወስደው በእስር በሚገኙበት ሁኔታ ሙስናን አጋልጡ፣ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ቆርጦ ተነስቷል ማለት ቀልድ “ ነው ብለዋል።
በቀረቡት ጥያቄዎች የተበሳጩት አስተዳዳሪው የተጠቀሱት ግለሰቦች የተያዙት የጦር መሳሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሰነዶችን ይዘው በመገኘታቸው ነው ፤ የህዝብን ኃሳብ ለመበታተን የሚደረግ ጥረት ራሱ ሙስና ነው ፡፡›› በማለት መልሰዋል።
ለሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማስፈጸሚያ እንዲያግዝ ሚያዝያ 14/2008 ዓ.ም ከመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ፣የመሰናዶ ት/ቤቶችና የማሰልጠኛ ተቋማት መምህራን ጋር ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገ ስብሰባ ላይ መምህራን በርካታ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
መምህራኑ “የዜጎች ክብርና መብት በማይከበርበት፣ ዜጎች በሥራ አጥነትና ፍትህ እጦት ለስደት በሚዳረጉበትና በሄዱበት ክብራቸው ከመገፈፉ አልፎ በሊቢያ ሲታረዱ፣ በደቡብ አፍሪካ ሲቃጠሉ፣ በተለያዩ አገራት ሲገደሉና ከፎቅ ሲወረውሩ ዓለም በሚያይበት እውነት ውስጥ፣ እንዲሁም በቅርቡ ከሁሉም በከፋ መጠን በጋምቤላ ዜጎች በስደት ባስጠጋናቸው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በአገራቸው እየተገደሉ ባሉበት ሁኔታ ለማን ስለሚደረግ ልማትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ነው የምትነግሩን ?” በማለት ትችትና ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
መምህራኑ “ በዞኑ በኢንቨስትመንት ስም የተዘረፈው መሬትና ሃብት ከ930 ሚሊዮን በላይ ብር ደርሶ እያለ ፣ ይህንኑ ገንዘብ ማስመለስና ለልማት ማዋል ሲቻል እናንተ እንደገና ገንዘብ አዋጡ ትሉናላችሁ” በማለትተቃውሞ አሰምተዋል። በዚሁ ዜና ላይ ከተሳታፊ መምህራን ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ በሚቀጥሉት ቀናት እንደሚኖረን ለመግልጽ እንወዳለን።