የደቡብ ሱዳን አውሮፕላን ተከስክሶ 19 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 5/2010) አንድ አነስተኛ የደቡብ ሱዳን አውሮፕላን ተከስክሶ የ19 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ አንዲት ሕጻንን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ከአደጋው መትረፋቸው ታወቀ።

ወንዝ ላይ ተከሰከሰ የተባለው አውሮፕላን ከደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ይሮል

ወደተባለ ሌላ የደቡብ ሱዳን ከተማ በመጓዝ ላይ እንደነበሩ ዘገባው አመልክቷል።

የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አንድ ሕጻንና ረዳት አብራሪውን ጨምሮ ሶስት ሰዎች በሕይወት ተርፈዋል።

በአደጋው የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ሁለት መኮንኖች እንዲሁም አንድ የሃይማኖት አባት ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

ስለ አውሮፕላኑ አደጋ ዝርዝር መረጃ እየተጣራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ አውሮፕላኑ መያዝ የሚገባው 19 ተሳፋሪዎችን ቢሆንም በጠቅላላ 22 ሰዎች በአውሮፕላኑ ውስጥ እንደነበሩ ታውቋል።

አውሮፕላኑ ወደ ማረፊያው ሲቃረብ የአየር ጸባዩ ጭጋጋማ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ለማረፍ በሚሞክርበት ወቅት ወንዝ ላይ መከስከሱ ተሰምቷል።

ትላንትና በተከሰከሰው በዚህ አነስተኛ አውሮፕላን አብራሪውን ጨምሮ 19 ሞተዋል።ረዳት አብራሪው አንድ ሕንጻን አንድ ጣሊያናዊ ዶክተር ደግሞ ከአደጋው በሕይወት መትረፋቸውን አልጀዚራ በዘገባው አመልክቷል።