የደመራ በአል ተከበረ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 16/2011) የዘንድሮው የደመራና የመስቀል በአል የሚከበረው ሰይጣን ድል በተነሳበትና ሁለቱ ሲኖዶሶች ወደ አንድነት በመጡበት ወቅት ነው ሲሉ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ ገለጹ።

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ይህንን መልዕክት ያስተላልፉት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በተከበረው የደመራ በአል ላይ ነው።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የደመራ በአል በስፍራው ለታደሙ ምዕመናንና እንግዶች መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ በሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ መፈጠሩንና ሁለቱም አባቶች በአንድነት ሆነው በአንድ ሃገር በአሉን ለማክበር መቻላቸው ትልቅ ሃሴት የሚፈጥር እድለኝነት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ሰይጣን ድል በተነሳበት ወቅት የሚከበር ታላቅ በአል ነው ሲሉም ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የደመራ በአል በዛሬው እለት በአዲስ አበባና በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል።

በዋሽንግተን ዲሲም 25 አብያተክርስቲያናት በአንድነት በመሆን በተመሳሳይ የደመራ በአል አክብረዋል።