የውጭው ሲኖዶስ ለሰላሙ ድርድር ዝግጁ ነኝ አለ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 6/2010) በብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራው በውጭ ሃገር የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰላሙ ድርድር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።

በእርቅ መድረኩ ላይ የሚገኙ ሶስት ሊቃነጳጳሳት መሰየማቸውንም ይፋ አድርጓል።

የጥላቻና የመከራው ዘመን ያብቃ ሲልም ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪውን አቅርቧል።

በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ በሚጀመረውና ከሐምሌ 12 እስከ 21 እንዲቀጥል መርሃ ግብር በተያዘለት የእርቅ ፕሮግራም እንዲሳካ ቅዱስ ሲኖዶሱ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ይፋ አድርጓል።

በፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራውና በውጭ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ እስከዛሬም በሩን ከፍቶ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውቋል።

በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶሱ በዋና ጸሃፊው አቡነ ሚካኤል ስም ያወጣው መግለጫ የጥላቻና የመከራው ዘመን አብቅቶ በኢትዮጵያ ሰላም ፍቅርና አንድነት ይሰፍን ዘንድም ምኞቱን ገልጿል።