የወልቃይትን ህዝብ የማፈናቀልና የማሳደድ ተግባር ይቁም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 23/2011)የወልቃይትን ህዝብ የማፈናቀልና የማሳደድ ተግባር እንዲቆም ልሳነ ግፉአን ጠየቀ።

ለወልቃይት ጠለምትና ጠገዴ የአማራ ተወላጆች መብት የሚቆረቆረው ልሳነ ግፉአን በህወሃት አገዛዝ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ላይ የሚደረሰውን የመብት ጥሰት በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።

ሰሞኑን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ከተለያዩ የወልቃይት አካባቢዎች መፈናቀላቸውን ተከትሎ ልሳነ ግፉአን የአማራ ክልልና የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አድርጓል።

የተፈናቀሉት ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እንዲደረግም ልሳነ ግፉአን ጠይቋል።

ባለፉት አራት ወራት በወልቃይት የአማራ ተወላጆች ላይ የተጠናከረ የመብት ጥሰት ሲፈጸም መቆየቱን ያወሳው ልሳነ ግፉአን ሰሞኑን ይሀው እርምጃ ተባብሶ ቀጥሏል ሲል ነው ያስታወቀው።

ድርጅቱ ለኢሳት በላከው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የለውጥ ሂደት እንዲደናቀፍና ዜጎች ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዲገቡ ትንኮሳዎችን በመፈጸም ላይ ያለው የህወሀት ቡድን የወልቃይት ጠለምት ጠገዴ ህዝብ ላይ የሽብር ተግባር በመፈጸም ላይ ነው ሲል አውግዟል።

የእኩይ ምግባሩ መገለጫ የሆነውን ህዝብ የማሰቃየትና የማፈናቀል እርምጃ በመውሰድ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ያደረገው የህወሀት ቡድን መጠነ ሰፊ የማወክ ዘመቻ መክፈቱን ነው ልሳነ ግፉአን በመግለጫው የጠቀሰው።

ባለፈው ሳምንት በተከበረው የመስቀል በዓል ላይ ምልክት የሌለበትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዛችኋል በሚል 15 ወጣቶች ላይ የአፈናና የእስራት እርምጃ መውሰዱን ልሳነ ግፉአን አስታውቋል።

በህወሀት ታጣቂዎች እየተፈጸመ ያለውን እስራትና አፈና በመሸሽ ከ150 በላይ የአማራ ተወላጆች ወደ ተለያዩ አከባቢዎች መሰደዳቸው ተገልጿል።

አብዛኞቹ በአማራ ክልል ስር በምትገኘው ሶሮቃ ወረዳ መግባታቸውም ታውቋል ይላል መግለጫው።

ከመስቀል በዓል በኋላ ባሉት ተከታታይ ቀናት እየተወስደ ያለው እርምጃ የቀጠለ መሆኑን የገለጸው ልሳነ ግፉአን አማራ ነን ካላችሁ ወደ አማራ ክልል ሂዱ የሚል አስገዳጅ መመሪያ በመምጣቱ ተጨማሪ ሰዎች በመፈናቀል ላይ ናቸው ብሏል።

እነዚህ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት በአርማጮህና ጠገዴ አከባቢዎች ህብረተስቡ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነም ተመልክቷል።

ይሁንንና የምግብ; የልብስና የውሃ እጥረት በመኖሩ ተፈናቃዮቹን ለማቆየት ችግር መግጠሙን ልሳነ ግፉአን ገልጿል።

መንግስት በአስቸኳይ ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲደርስም ጥሪ አድርጓል።

በመሆኑም በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን ተፈናቃይ ቁጥር ለመግታት የአማራ ክልልና የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ በመግባት በወልቃይት የአማራ ተወላጆችን ድህንነትና ሰላም እንዲያስጠብቁ ልሳነ ግፉአን ጠይቋል።

ባለፈው ሳምንት ታፍነው ወደ እስር ቤት የተወሰዱ የአማራ ተወላጆች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የጠየቀው ልሳነ ግፉአን፡ መንግስት ለተፈናቀሉትም ሆነ አደጋ ላይ ለሚገኙት ዜጎች የደህንነት ሙሉ ዋስትና መስጠት እንደሚገባው አሳስቧል።

በዘላቂነትም የክልልና የፌደራል መንግስታት ለወልቃይት ጠለምት ጠገዴ ማህበረሰብ የአማራ ማንነት ጥያቄ መልስ በመስጠት የተራዘመውን የህዝባችንን መከራ እንዲያስቆም እንጠይቃለን ብሏል ልሳነ ግፉአን።