የካቢኔ አባላት ሹመት ተሰጠ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 4/2010) የአዲስ አበባ ምክር ቤት አዳዲስ የካቢኔ አባላት ሹመት ሰጠ።

ምክር ቤቱ ሹመቱን የሰጠው የካቢኔ አባላትን በመበወዝ መሆኑም ታውቋል።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሹመቱ ብቃትንና ኢትዮጵያዊነትን ብቻ መሰረት ያደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።

በአዲሱ የካቢኔ ድልድል በቅርቡ የብሔራዊ ቲያትር ስራ አስኪያጅ ሆኖ የተሾመው አርቲስት ነብዩ ባዬ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሆኖ ተሹሟል።

በዚህም የብሔራዊ ቲያትር ስራ አስኪያጅነትን ቦታውን ስለሚለቅ በምትኩ ሌላ ሰው ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።

አፈጉባኤ የነበሩት ዶክተር ታቦር ገብረመድህን ከቦታቸው ተነስተው ወደ ትምህርት ቢሮ ሃላፊነት ሲዛወሩ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ አፈጉባኤ ሆነው ተሾመዋል።

በአጠቃላይ 20 ያህል የካቢኔ አባላትን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት አቅርበው ያስጸደቁት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሹመቱ ኢትዮጵያዊነትንና ብቃትን ብቻ መሰረት ያደረገ እንደሆነም አመልክቷል።