የኦነግ ወታደሮች ራሳቸውን እንዲከላከሉ ትዕዛዝ ተሰቷቸዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2011) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወታደሮች ጥቃት ከተፈጸመባቸው ራሳቸውን እንዲከላከሉ ትዕዛዝ ሰጥተናል ሲሉ አቶ ዳውድ ኢብሳ ገለጹ።

          በትላንትናው ዕለት ኦዴፓ ያወጣውን መግለጫምየጦርነት አዋጅ ነው ያሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ የመንግስት ሰራዊት በዛሬው እለት ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው ሲሉምተናግረዋል።

          አዲስ አበባ በሚገኘውና በቅርቡ በመንግስት በተሰጣቸው ጽሕፈት ቤት መግለጫ የሰጡት አቶ ዳውድ ኢብሳ በዛሬው ዕለት ዶክተር ገዳን ጨምሮ የተወሰኑ የኦነግ አባላት ከድርጅቱ ጽሕፈት ቤት መያዛቸውን ገልጸዋል።

          የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/በኢትዮጵያ ውስጥ ከ8 ወራት በፊት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በድርድር ወደ ሃገር ቤት ከገባ አራት ወራት ያስቆጠረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱን በይፋ አስታውቋል።

          የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ዛሬ አዲስ አበባ ኦነግ ጽህፈት ቤት በሰጡት መግለጫ ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ሰራዊት በባሌ፣በጉጂና በወለጋ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ብለዋል።

          ሰራዊታችን ጥቃት አይፈጽምም ያሉት የኦነጉ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ራሱን እንዲከላከል ግን ትዕዛዝ ሰተናል ብለዋል።

          ትላንት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኦዴፓ/ጦርነት የሚመስል አዋጅ አውጆብናል ያሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ የወጣው መግለጭእም ይህንኑ ያጠናክራል ብለዋል።

          አስመራ ላይ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ አልሆነም ብለዋል።

          ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ከጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰአረ መኮንንና ከጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ሃላፊው ጄኔራል አደም ኢብራሒምና ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሑሴን ጋር ያደረግነው ስምምነትም አልተተገበረም ሲሉም ገልጸዋል።

          በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ በኦነግ አባላትና በኦሮሞ ሕዝብ ትግል ነው ያሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲካሄድም ጥሪ አቅርበዋል።