የኦነግ አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ህብረተሰቡን መሳሪያ እያስፈቱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 7/2011)የኦነግ አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ህብረተሰቡን መሳሪያ እየነጠቁ መሆናቸው ተገለጸ።

በህጋዊ መንገድ ከመንግስት ፍቃድ ተሰጥቶን የታጠቅነውን መሳሪያ የኦነግ ታጣቂዎች ነን ባሉ ሃይሎች እየተወሰደብን ነው ሲሉ በወለጋ ቆሪና ሚንኮሎንጫ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ፋይል

ነዋሪው ጥቃት ይደርስብናል በሚል ስጋት አከባቢውን ለቆ በመውጣት ላይ እንደሆነም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በኦነግ ሰራዊት የመሳሪያ ነጠቃው መፈጸሙን በተመለከተ ከአመራሮች ምላሽ ለማግኘት ያአረግነው ጥረት አልተሳካም።

ባለፈው ሳምንት በቤንሻንጉል ወታደራዊ ሰፈር አቋቁሞ ስልጠና በሚሰጥ የተደራጀ ቡድን ላይ መንግስት እርምጃ መሰዱን መግለጹ የሚታወስ ነው።

በቤንሻንጉል ጉምዝ በኦነግ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈጸም የክልሉ ፖሊስ ማስታወቁ ተገልጿል።

መሳሪያ እንዲፈታ በመንግስት በኩል እየተጠየቀ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ህብረተሰቡን ትጥቅ እያስፈታ መሆኑን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ኢሳት ያነጋገራቸው የወለጋ ቆሪና ሚንኮሎንጫ ነዋሪዎች እንደሚሉት የኦነግ ወታደሮች ነን ያሉና አርማውን አንግበው የመጡ ታጣቂዎች ህብረተሰቡን መሳሪያ እየነጠቁ በመውሰድ ላይ ናቸው።

መንግስት ያስታጠቀንን ኦነግ የሚያስፈታን ምክንያት አልገባንም ያሉት ነዋሪዎች አስገዳጅ የሆነው የመሳሪያ ነጠቃ በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ለኢሳት ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ የኦነግ ሰራዊት ናቸው ባሏቸው ታጣቂዎች እየተወሰደ ባለው የመሳሪያ ነጠቃ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተናል፡ ቀጣዩ ርምጃ በማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት ሊሆን ይችላል ሲሉ ገልጸዋል።

ከወዲሁ ከቆሪና ሚንኮሎንጫ ከተባሉ አካባቢዎች ከ1ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሸሻቸውንና አዋሬ በሚባል ቦታ ተጥልለው እንደሚገኙ የሚገልጹት ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት እየደረሰብን ያለውን ጥቃት መከላከል አልቻለም በማለት ምሬታቸውን ይገልጻሉ።

ኢሳት በወለጋ ነዋሪውን ትጥቅ እያስፈታ ያለው የኦነግ ሰራዊት ነው መባሉን በተመለከተ የግንባሩን አመራሮች ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በተያያዘ ዜናም በምዕራብ ወለጋ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የኦነግ ታጣቂዎች ህብረተሰቡን ትጥቅ በማስፈታት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በስየ ወረዳ ነዋሪ ከሆኑና በመንግስታ ፍቃድ አግኝተው መሳሪያ ከታጠቁት ላይ ኦነግ እያስፈታ በመውሰድ ላይ መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

የቆሪና ሚንኮሎንጫ አካባቢ ነዋሪዎች መልዕክት አላቸው። በስጋት ላይ ስለሆንን መንግስት ይድረስልን የሚል።