የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አዋጅ አወጀ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አዋጅ አወጀ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 5 ቀን 2010 ዓ/ም ) በኦቦ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ጋ ለረዥም ዓመታት ሲያደርገው የነበረው የሰላም ጥሪ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን በማስታወስ፣ በቅርቡ በግንባሩ ሊቀመንበር እና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መካከል በተደረገ ውይይት የሰላም ድርድሩ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄዱን አብራርቷል።
ኦነግ ችግሩን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የደረሰበትን ውሳኔ መንግስታት፣ሕዝቦችና ሰላም ወዳድ ኃይላት ሁሉ የሚሹት እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል።
በመሆኑም የተጀመረውን የሰላም ድርድር ወደፊት ለማራመድ ይረዳል ከሚል እምነት ከመንግስት ኃይላት የሚፈጸምበትን ጥቃት ከመከላከል ውጭ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለማድረግ መወሰኑን ያወጀው ኦነግ፣የሰላም ውይይቱ ፍሬ እንደርሚያፈራና የኢትዮጵያ መንግስትም ተመሣሳይ የተኩስ አቁም እንደሚያውጅ ያለውን እምነት ገልጿል።
በዚህ መሰረት የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ እንዲሆን ለግንባሩ ሥራ አስፈጻሚዎች በሙሉ ትዕዛዝ መተላለፉን ኦነግ አስታውቋል።