የእስራኤል ፖሊስ አንድ ኢትዮጵያዊን ወጣትን መግደሉ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 21/2011)የእስራኤል ፖሊስ አንድ የአዕምሮ ሕመም ያለበትን ኢትዮጵያዊ በመግደሉ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቁጣን አስነሳ።

የሁዴ ቢያድጌ የተባለው የ24 ዓመት ወጣት ኢትዮጵያዊ ከቤቱ ወጥቶ ሲሄድ ቤተሰቦቹ ለፖሊስ ይደውላሉ።

ቤተሰቦቹ ፖሊስ የጠሩበት ምክንያት ልጃቸው አደጋ እንዳይደርስበት እንዲታደግላቸው እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።

ይሁንና ፖሊስ ከተጠራ በኋላ የአዕምሮ ህመምተኛው ጩቤ ይዟል በማለት ተኩሰው እንደገደሉት ለማወቅ ተችሏል።

የአዕምሮ ሕመምተኛው ኢትዮጵያዊ እገዛ ሊደረግለት ሲገባ በፖሊስ በመገደሉ በአካባቢው በሚገኙ ነዋሪዎች ዘንድ ቁጣን መፍጠሩ ተነግሯል።

በእስራኤል ቴልአቪቭ አዝራይሊ በተባለ መስቀለኛ መንገድ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ መዘጋጀታቸው ተዘግቧል።

የሟቹ ቤተሰቦች ልጃቸውን እንዲታደግልቸው ፖሊስ ስለጠሩ በተቃራኒው ሆኖ በማግኘታቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

የእስራኤል ፖሊስ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ማብራሪያ የለም።