የኤርትራው መሪ ቅዳሜ አዲስ አበባ እንደሚገቡ መንግስት አስታወቀ

የኤርትራው መሪ ቅዳሜ አዲስ አበባ እንደሚገቡ መንግስት አስታወቀ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 6 ቀን 2010 ዓ/ም ) የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት ቅዳሜ የሚገቡት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በአዲስ አበባና በሃዋሳ የስራ ጉብኝት ያካሂዳሉ። የሁለቱ አገራት መሪዎች በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው የሁለቱን አገራት ሰላም እንደሚያበስሩ ሃላፊው ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክንም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዶ/ር አብይ አህመድ ኤርትራን በጎበኙ በሳምንታቸው የኤርትራው መሪ ኢትዮጵያን በይፋ መጎብኘታቸው ሁለቱ አገራት ሰላም በማውረድ በጋራ ለማስራት ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል። ባለፉት 20 አመታት በነበረው ሁኔታ ሁለቱም አገራት መጎዳታቸውን ያመኑበትና የጠፋውን ጊዜ ለመካስ እሩጫ መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው በማለት ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።