የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከመቼው በላይ ዝቅተኛ ነው ተባለ

ሰኔ 9 ፥ 2009

የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከመቼው ጊዜ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። ዘርፉ እያበረከተ ያለው አስተዋጽዖም ባለፉት 40 በላይ አመታት እጅግ ዝቀተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

ጋዜጣው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ለአገሪቷ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከሁሉም የአፍሪካ ሃገራት እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገቡን የአለም ባንክን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል። በመሆኑም፣ መስኩ እኤአ በ2015 ከአገሪቱ አጠቃላይ ገቢ 4.5 በመቶ የሆነውን ያስመዘገበ ሲሆን፣ እኤአ በ 1997 ከነበረው ከ7.8 ፐርሰንት አሽቆልቁሎ ታይቷል።

ፋይናንሻል ታይምስ እንደገለጸው ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ካሜሩን፣ ቤኒን፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክና ዚምባብዌ ከዘርፉ 10 ፐርሰንት ያክል ገቢ እንደሚያገኙበት የተገለጸ ሲሆን፣ ናይጀሪያና ኡጋንዳም ከተጠቀሱት አገራት ተርታ እንደሚገኙ አትቷል።

አፍሪካ ከማኑፋክቸሪንግ የምታገኘው አጠቃላይ ገቢ 10.6 ፐርሰንት የደረሰ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ተለይቶ ወደ 4.5 አካባቢ መቀነሱ ጥያቄ ማስነሳቱን ጋዜጣው ባለሙያዎችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

“ካየናቸው አገራት ኢትዮጵያ በጣም አነስተኛ የማኑፋክቸሪንግ ይዞታ ያላት አገር ናት ያሉት የሬኔሳይንስ ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ሃላፊ ቻርልስ ሮበርትሰን፣ መሬት ላይ የሌለ የህዝብ ግንኙነት ስራ በመንግስት ተሰርቷል” ሲሉ ለጋዜጣው ተናግረዋል። ሌላው “አፍሪካ ኢኮኖሚክስ” በሚባል ኩባንያ ውስጥ የሚሰሩ ጆን አሽበርን የተባሉ ኢኮኖሚስት፣ የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን በተመለከተ በመገናኛ ብዙሃን የሚወራው ወሬ የተጋነነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፉ ከሌሎች የአፍሪካ አቻ ሃገራት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በልጽጋለች ሰለሚባለው ጉዳይ በተመለከተ፣ እኤአ በ 2015 አም ሃገሪቱ 44 ሚሊዮን የሚጠጋ የጫማ ምርቶችን ወደ ውጭ የላከች ሲሆን፣ ቬይትናም ከላከችው ሩብ እጅ ብቻ እንደሚሆን ፋይናንሻል ታይምስ ገልጿል። አጠቃላይ ከምስራቅ አፍሪካ ወደውጭ ኤክስፖርት የተደረገው የጨርቃጨርቅ ምርት፣ የቡና ምርትን አንድ አስረኛ እንደሚሆን መጽሄቱ ጨርሞ ገልጿል።