የኢትዮጵያ ፓስፖርት ከአፍሪካ የመጨረሻዎቹ አምስት ሀገራት ውስጥ ተመደበ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 15/2010)የኢትዮጵያ ፓስፖርት ከአፍሪካ የመጨረሻዎቹ አምስት ውስጥ ሲመደብ ከአለም ደግሞ 185ኛ በመሆን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን ፓስፖርት ኢንዴክስ ይፋ ያደረገው አዲስ ሪፖርት አስታወቀ።

የሀገራትን የጉዞ ሰነድ ወይንም ፓስፖርት ጥንካሬ የሚገመግመው ፓስፖርት ኢንዴክስ ይፋ ባደረገው በዚህ አዲስ ጥናት ከአለም ሲንጋፖር ቀዳሚ ሆና ስታልፍ ከአፍሪካ ሲሸልስ የመሪነቱን ቦታ ይዛለች።

የየሀገራቱን ፓስፖርት በመያዝ ያለቪዛና አየር ማረፊያ ሲደርሱ በሚመታ ቪዛ በአለም ላይ ወደ 159 ሀገራት በነጻነት በመንቀሳቀስ የሲንጋፖር ፓስፖርት ቀዳሚ ሆኖ ተመዝግቧል።

በጀርመን ፓስፖርት 158 ሀገራት በሲውዲንና ደቡብ ኮሪያ ፓስፖርት 157 ሀገራት በመጓዝ ተጠቃሾቹ ሀገራት ከአለም ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል።

በብሪታኒያ፣ፈረንሳይ፣ጣሊያንና ጃፓን ፓስፖርቶች በ156 ሀገራት በነጻነት መንቀሳቀስ የሚቻል ሲሆን የአውስትራሊያ፣ስዊዘርላንድ፣የቤልጂየምና የኔዘርላንድ ፓስፖርት ወደ 155 ሀገራት በማስጓዝ በ5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

የአሜሪካና የካናዳ ፓስፖርቶች 154 ሀገራትን በነጻነት የሚያንቀሳቅሱ በመሆናቸው የ6ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ከአፍሪካ ግንባር ቀደም በሆነችውና ከአለም በ29ኛ ደረጃ ላይ ባለችው ሲሸልስ ፓስፖርት 130 ሀገራት በነጻነት መንቀሳቀስ የሚቻል ሲሆን ከአፍሪካ 2ኛና 3ኛ በሆኑት ሞሮሺየስና ደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት 124ና 93 ሀገራትን በነጻነት መንቀሳቀስ የሚያስችል መሆኑን ከፓስፖርት ኢንዴክስ የ2017 አዲስ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።

ጎረቤት ሀገር ኬንያ ከአለም በ120ኛ ደረጃ ከአፍሪካ ደግሞ 8ኛ ስትሆን በኬንያ ፓስፖርት 68 ሀገራትን መጓዝ የሚቻል መሆኑንም አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 51ኛ ከአለም ደግሞ 185ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በኢትዮጵያ ፓስፖርት 39 ሀገራት መጓዝ ሲቻል ከኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ በምትገኘው ኤርትራ ፓስፖርት 39 ሀገራት መጎብኘት ይቻላል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ በአንድ ደረጃ ከፍ ያለችው የኤርትራ ፓስፖርት በቀጥታ ያለምንም ቪዛ የሚገባባቸው ሀገራት 10 ሲሆኑ የኢትዮጵያ 9 ናቸው።

በአፍሪካ ውስጥ ከኢትዮጵያ በታች የተቀመጡት ሶስት ሀገራት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ሊቢያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ናቸው።

በሊቢያ ፓስፖርት 38 ሀገራትን፣በሱዳን 36 እንዲሁም በሶማሊያ ፓስፖርት ደግሞ 34 ሀገራትን ያለ ቪዛ መጎብኘት ይቻላል።

በአለም ላይ የመጨረሻ ሆና በተመዘገበችው አፍጋኒስታን ፓስፖርት 24 ሀገራት ያለቪዛ መጎብኘት እንደሚቻል ከፓስፖርት ኢንዴክስ አመታዊ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።