የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያቋቋመችው ባንክ እንዲመዘገብ ጠየቀች

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 26/2010)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከትግራይ ባለሃብቶች ጋር በመሆን ያቋቋመችው  ባንክ እንዲመዘገብ ለብሔራዊ ባንክ ማመልከቻ አቀረበች።

ከብሔራዊ ባንክና ከቤተክህነት ምንጮች በሰነድ ተደግፎ ለኢሳት ከደረሰው መረጃ መረዳት እንደተቻለው የባንኩን ድርሻ 63 በመቶ የትግራይ ባለሃብቶች፣19 በመቶ ቤተክህነት ሲይዙ ቀሪው 18 በመቶ ትንንሽ አክሲዮን ለሚገዙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሽያጭ ቀርቦ ተሸጧል።

“ዳሎል” በሚል ስያሜ በመቋቋም ላይ ያለው ባንክ ቤተክርስቲያኒቱ በልዩ ልዩ ባንኮች ያስቀመጠችው 12 ቢሊየን ብርን በመጠቀም ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱንም የቤተክርስቲያኒቱ ምንጮች ገልጸዋል።

ይህም የቤተክርስቲያኒቱን ሃብት ለአደጋ ያጋለጠ ርምጃ እንደሆነም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ 17ኛው የግል ባንክ ለመሆን በመንቀሳቀስ ላይ ያለው ዳሎል ባንክ የባንኩን 63 በመቶ ድርሻ የትግራይ ባለሃብቶችና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጋራ ይዘውታል።

ቀሪውን 18 በመቶ ለመሸጥ በአደባባይ ጥሪ ያቀረቡት ባለፈው ታህሳስ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።ከዚህ ወስጥ በላይነህ ክንዴ የተባሉ የአማራ ባላሃብት ከፍተኛ አክሲዮን ሲገዙ የቀረውን ከ200 በላይ ሰዎች በአነስተኛ ተከፋፍለውታል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች በሚሰጥ  አስራትና አብያተክርስቲያናቱ ከህንጻ ኪራይና ከመሳሰሉት በሚያገኙት ገቢ በተለያዩ ባንኮች የተቀመጠ  የቤተክርስቲያኒቱ ገቢ 12 ቢሊየን ብር ያህል እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

ጠቅላይ ቤተክህነት ይህንን ሃብት በመያዝ የግል ባንክ ለማቋቋም በተንቀሳቀሰበት ወቅት ብሔራዊ ባንክ ለሃይማኖት ተቋማት የባንክ ፈቃድ እንደማይሰጥ በመግለጹ ከትግራይ ባለሃብቶች ጋር ግንኙነት መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል።

ይህንን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግና እንቅፋት እንዳይገጥመው ከሕወሃት ባለስልጣናት ከተሰጠ ድጋፍ ባሻገር የብሔራዊ ባንክ ገዢው አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ወንድም አቶ መንግስቱ አጥናፉ በዋና አደራጅነትና አማካሪነት እየሰሩ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

የመንበረ ፓትሪያርኩ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት እያንዳንዳቸው በ25ሺ አክሲዮን 25 ሚሊየን ብር በድምሩ 50 ሚሊየን ብር ለደሎል ባንክ አዋጥተዋል።ብጹእ  አቡነ ዲዮስቆሮስ የመንበረ ፓትሪያርኩ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትን ሲወክሉ መምህር ጎይቶም ያይኑ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከትን መወከላቸውንም ከሰነዱ መረዳት ተችሏል።

ደብረጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያንና ማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን እያንዳንዳቸው 12 ሺ አክሲዮን መግዛታቸውንና ይህም በገንዘብ ሲተምን የእያንዳንዱ 12 ሚሊየን ብር መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

ደብረአሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን፣ሐመረ ኖህ ኪዳነምህረት ገዳም፣መንበረጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል፣ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም መካነ ቅዱሳን አንድነት፣ቦሌ ደብረምህረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከአንድ ሚሊዮን እስከ 10 ሚሊየን ብር አክሲዮን መግዛታቸው ታውቋል።

ምስካየ ሕዙናን መድሃኒአለም ገዳም፣ሲ ኤም ሲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንና ጸርሃ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ደግሞ ከመቶ ሺ እስከ 200 ሺ ብር አክሲዮን በመግዛት በዝቅተኛ መጠን ተሳታፊ ሆነዋል።

ቤተክርስቲያኒቱ ካሏት 13ሺ ያህል አብያተክርስቲያናት አስራ ሁለቱ ቤተክርስቲያናትና ሁለቱ ጽህፈት ቤቶች ብቻ የተመረጡበት መመዘኛም ሆነ ምክንያት በግልጽ አልተነገረም።

ሆኖም የቅርብ ምንጮች እንደሚገልጹት የዚህ አላማ በባንኩ ውስጥ የትግራይ ባለሃብቶችን ድርሻ ከፍ በማድረግ ይበልጥ ባለቤትነቱን ወደነሱ ለማድረግ የታለመ እንደሆነም ይገልጻሉ።

ባንኩ ውጤታማና ትርፋማ እንዲሆን ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ባንክ ነው በሚል ጠቅላላ ሃብቱን 12 ቢሊየን ብር በሃገሪቱ ካሉት ልዩ ልዩ ባንኮች ወደዚህ ወደ ዳሉል ባንክ ለማዛወር መታቀዱም ተሰምቷል።

በዚህ የዳሎል ባንክ ውስጥ ቤተክህነት 19 በመቶውን ስትይዝ የአምበሳውን ድርሻ 63 በመቶ በመያዝ የትግራይ ባለሃብቶች በቤተክርስቲያኒቱ ገንዘብ ለመንቀሳቀስ ተዘጋጅተዋል በሚል የቤተክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪዎች ለምዕምናኑ ሃብታቸውን እንዲጥብቁ ጥሪ አቅርበዋል።በሰነዱ ላይ ስማቸው የተዘረዘረው 16 የትግራይ  ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ብሔራዊ ባንክ ከሚጠይቀው ግማሽ ቢሊየን ብር የ328 ሚሊየን 801 ሺ ብር ድርሻ ይዘዋል።

አቶ አዘዞም አየለ፣አቶ ሃይለስላሴ አምባዬ፣አቶ ብርሃኔ ግደይ፣አቶ አትክልቲ ይህደጎ፣አቶ ታደሰ ደስታ፣አቶ ሙለይ አዲስ፣አቶ ሃጎስ ሃድጉ ገብረእግዚአብሔር እንዲሁም ሙሉ ታምራት እያንዳንዳቸው በ25 ሺ አክሲዮን በግል የ25 ሚሊየን ብር ባለድርሻ መሆናቸውን ለብሔራዊ ባንክ ከቀረበው ሰነድ ላይ መመልከት ተችሏል።

ተካሃፍ ትሬዲንግ፣ታምሪን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ፣ቢ ኤን ቲ ኢንደስትሪ ኤንድ ትሬዲንግ፣ወርቃ ትሬዲንግ ሃውስ የተባሉ የትግራይ ባለሃብቶች ኩባንያዎችም እያንዳንዳቸው በ25 ሺ አክሲዮን እያንዳንዱ ኩባንያ የ25 ሚሊየን ብር ባለድርሻ መሆኑንም  መረዳት ተችሏል።

አቶ አዲስ ገብረማርያም፣ሙሉ ሚዛን ትሬዲንግ፣አቶ በርሔ ሃጎስ፣ሉችያ ተስፋዬ ገብረመስቀል ደግሞ ከ5 ሚሊየን ብር እስከ 12 ሚሊየን 500 ሺ ብር አክሲዮን መግዛታቸውን መረዳት ተችሏል።

ከዳሎል ባንክ ውስጥ 328 ሚሊየን 801ሺ ብር የ16 የትግራይ ተወላጆችና ኩባንያዎች ድርሻ ሲሆን ፣19 በመቶው የቤተክህነት ድርሻ ከነሱ ጋር በትብብርና በቁርኝት የሚሰሩት እነ መምህር ጎይቶም የተወከሉበት እንደሆነም ተመልክቷል።

ከባንኩ የአክሲዮን ድርሻ ቀሪው 18 በመቶ፣ከታህሳስ ወር ጀምሮ በይፋ ለገበያ የቀረበ ቢሆንም በግለሰብ ደረጃ 220 ሰዎች አክሲዮን የገዙ ሲሆን ጠቅላላ ድርሻቸው 17 ሚሊዮን 290ሺ ሆኗል።ይህም የ220ዎቹ ባለአክሲዮኖች ድርሻ ከአንድ የትግራይ ባለሃብት የነሰ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

ባንኩ የትግራይ ተወላጆች ባንክ ነው የሚለውን ጥያቄና ተቃውሞ ለመከላከል እስከ 12 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለሌሎች ኩባንያዎች መልቀቁም ተመልክቷል።

ከትግራይ ወጭ የሆኑትና ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው በላይነህ ክንዴ የተባሉ ባለሃብት መሆናቸውንም ሰነዱ ያስረዳል።

በሀገሪቱ ካሉት ባንኮች አንበሳ ባንክ በትግራይ ተወላጆች የሚመራ ሲሆን። ወጋገንም የህወሃቱ ኤፈርት ከፍተኛ ድርሻ ያለበት ባንክ መሆኑም ይታወቃል።