የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ የእርሻ መሬት እንዳይታረስ ተከለከለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2011) የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ የሚጠቀምበት የእርሻ መሬት እንዳይታረስ መከለከሉ ተገለጸ።

በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ወረዳ ኩየራ አቅራቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ በአከባቢው ወጣቶች መሬቱ ይገባናል የሚል ጥያቄ በመነሳቱ የዘንድሮው የእርሻ ዘመን መቅርቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ የቆየው ኮሌጁ ለዘመናት የሚጠቀምበት የእርሻ መሬት በህገወጥ መንገድ መታገዱን አስመልክቶ የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት መፍትሄ እንዲሰጡ ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሻሸመኔ ወረዳ አመራር ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ኮሌጁ የያዘውን ሰፊ መሬት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እልባት ለመስጠት እየተሞከረ ነው ብለዋል።

ከአዲስ አበባ በ235 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ሻሸመኔ ለመድረስ 25 ኪሎሜትር ሲቀር ኩየራ በምትባል አነስተኛ መንደር አቅራቢያ በ182 ሄክታር መሬት ላይ የተመሰረተ ነው።

በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1950 ዓመተምህረት መቋቋሙን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ላለፉት 60 ዓመታት የአዳሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የቀለምና የመለኮት ትምህርት በመስጠት አያሌ ምሁራንን ማፍራት የቻለ አንጋፋ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ በ1964 ዓመተ ምህረት በኮሌጅ ደረጃ አድጎ ለአካባቢው ማህበረሰብና በአጠቃላይ ለመላው ኢትዮጵያውያን አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ እንደሆነም ስለኮሌጁ በተጻፈ የታሪክ ድርሳን ላይ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ቀደምት ከሆኑና በአዳሪነት የላቀ የትምህርት አገልግሎት በመስጠት አሻራቸውን በማሳረፍ ከሚጠቀሱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምት ዋንኛው ሆኖ ይጠቀሳል።

ከመለኮታዊ ትምህርት በተጨማሪ በእርሻ በምህንድስና በቢዝነስና አካውንቲንግ የትምህርት ዘርፎች እስከ ዲግሪ መርሃ ግብር በመስጠት የሚታወቅ ተቋም ነው።

በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በቢዝነስ አድሜንስትሬሽን በማስተርስ ደረጃ እንዲያስተምር እውቅና ማግኘቱም ተመልክቷል።

ይህ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ዛሬ ላይ ችግር ገጥሞታል ይላሉ የኢሳት የመረጃ ምንጮች።

ኮሌጁ በይዞታነት የያዘውና ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ሲጠቀምበት የነበረው የእርሻ መሬት ዘንድሮ ሳይታረስ ጦሙን መክረሙን የሚጠቅሱት የመረጃ ምንጮች ለኮሌጁ በገቢ ምንጭነት ጭምር የሚያገለግለው እርሻ በአካባቢው ወጣቶች በተነሳ ጥያቄ ምክንያት መቆሙን ገልጸዋል።

የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት የሃይማኖት ግጭት መልክ እንዲይዝ በሚፈልጉ ሃይሎች ጠንሳሽነት የኮሌጁን ህልውና አደጋ ላይ የሚከቱ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው።

የእርሻ መሬቱ ይገባናል ያሉ የአካባቢው ወጣቶች በፈጠሩት ተቃውሞ የዘንድሮ የእርሻ ዘመን ሳይታረስ መቅረቱን ለማወቅ ተችሏል።

ወጣቶቹ ጥያቄያቸውን ከማቅረብ አልፈው መሬቱ እንዳይታረስ እገዳ መጣላቸው ስርዓት አልበኝነት መንሰራፋቱን የሚያሳይ ነው ሲሉ ኢሳት ያነጋገራቸው የኮሌጁ ማህብረሰብ አባላት ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን የመንግስት ሃላፊዎች፣የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ለማነጋገር ያለፈው እሁድ የተደረገው ጥረት የሻሸመኔ ወረዳ አመራሮች የተደረገላቸውን ጥሪ ባለመቀበላቸው ሳይደረግ መቅረቱም ታዉቋል።

ኮሌጁ በዚህም የተነሳ ህልውናው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ነው የተገለጸው።

ኢሳት የሻሸመኔ ወረዳ አመራሮችን ለማግኘት ባደረገው ጥረት መረጃ ለመስጠት ብቻ ፍቃደኛ የሆኑና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ አመራር ኮሌጁ በስፋት የያዘውን የእርሻ መሬት ከፍትሃዊነትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተገናዘበ መልኩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አድቬንቲስት ኮሌጅ ማህበረሰብ ግን በጉዳዩ ላይ የፌደራል መንግስቱ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።