የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምላሽ ሰጠ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 2/2011)በማንነቴ በደረሰብኝ ጥቃት አየር መንገዱን ለቅቄ ወደ ግብርና ገብቼአለሁ በሚል በአማራ ቴሌቪዥን ለተናገሩት ግለሰብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምላሽ ሰጠ።

በዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወለደ ገብረማርያም ፊርማ በተሰጠ ምላሽ የአማራ ቴሌቪዥን አየር መንገዱን ይቅርታ እንዲጠይቅም ያሳስባል።

ከባርነት ነጻነት ሞትን እመርጣለሁ በሚል ርዕስ በአማራ ቴሌቪዥን በቀረበው ዘገባ ካፒቴን ዮሀንስ ተስፋዬ በማንነቱ የሚደርስበት በደልና ስቃይ ከፍተኛ በመሆኑ መቀጠል ባለመቻል ስራውን መልቀቁን ይገልጻል።

አየር መንገዱ በጻፈው ደብዳቤ የአማራ ቴሌቪዥን ያቀረበው ዘገባ ሚዛናዊ ያልሆነና የሀሰት መረጃ የቀረበበት ነው ሲል ይከሳል።

ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ፕሮግራሙ የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ስለአንድ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባልድረባ ዘገባ ያቀርባል።

ዘገባው ካፒቴን ዮሀንስ ተስፋዬ የተባሉ የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ በማንነቴ በሚደርስብኝ በደልና ጭቆና ስራዬን በገዛ ፍቃዴ ለቅቄ ወደ ግብርና ስራ ገባሁ የሚል ነበር።

ለ1200 ሰዓታት እንደበረሩ የሚገልጹት ካፒቴን ዮሀንስ የሀገር ውስጥን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ በተለያዩ ሀገራት እንደበረሩ የሚገልጹት ካፒቴን ዮሀንስ በአየር መንገዱ ውስጥ የሚፈጸመውን ማንነት ላይ ያተኮረ በደል በዝርዝር ያስረዳሉ።

ካፒቴን ዮሀንስ እንደሚሉት በአየር መንገድ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ በአማራ ማንነታቸው ከፍተኛ በደል ተፈጽሞባቸዋል።

በማንነት ላይ የሚደርሰው አሸማቃቂ የሆኑ ነገሮችን ለመሸሽ በሚል ስራውን ትተው ወደ ትውልድ ቦታቸው ጎጃም መሄዳቸውንና በግብርና ስራ መሰማራታቸውን ነው ለአማራ ክልል ቴሌቪዥን የገለጹት።

ከአየር መንገዱ ይልቅ በግብርናው ላይ ነጻነት ይሰማኛል ያሉት ካፒቴን ዮሀንስ ከባርነት ሞትን እመርጣለሁ ሲሉ በአየር መንገዱ የደረሰባቸውን በደል በምሬት ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜም በጎጃም ደጀን በግብርና ሙያ ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙ በዘገባው ተገልጿል።

የካፒቴን ዮሀንስ ታሪክ በአማራ ቴሌቪዥን ከቀረበ በኋላ ከፍተኛ መነጋጋሪያ ሆኖ ነው ያለፉትን ሁለት ቀናት የቆየው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቲውተር ገጹ ጉዳዩን ያስተባበለ ሲሆን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚም ለአማራ ቴሌቪዥን የተቃውሞ ደብዳቤ ልኳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በጻፉት ደብዳቤ የአማራ ቴሌቪዥን ላቀረበው ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳስበዋል።

አቶ ተወልደ በደብዳቤአቸው ካፒቴን ተሾመ ረዳት አብራሪ እንጂ ዋና አብራሪ ባለመሆኑ ካፒቴን ተብሎ የተገለጸው ሀሰት ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ረዳት አብራሪ በሚል የገለጿቸውን የድርጅታቸውን የቀድሞ ሰራተኛ በአቅም ማነስና ስልጠና ላይ ድክመት በማሳየት ተደጋጋሚ ችግር የተከሰተባቸው መሆኑን አቶ ተወልደ በደብዳቤአቸው ይገልጻሉ።

በማንነቴ በደረሰብኝ የሚለው ክስ ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ ተወልደ የአማራ ቴሌቪዥን የአየር መንገዱ ስምና ዝና በሚያጎድፍ ዘገባ ላይ በመሰማራቱ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባዋል ብለዋል።

አየር መንገዱ የካፒቴን ዮሀንስን የስልጠና ውጤት የተመለከቱ የግል ማስረጃዎችን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ የለጠፈ ሲሆን ይህ የግልሰብ ማስረጃን በአደባባይ ማውጣት ተገቢ አይደለም የሚል ተቃውሞ እየተሰማ ነው።

ኢሳት በየጊዜው ከአየር መንገዱ የሚለቁ ሰራተኞችን በተመለከተ በርካታ ባለሙያዎችን ያነጋገረ ሲሆን አብዛኞቹ ድርጅቱን የሚለቁት በአየር መንገዱ ባለው ስር የሰደደ ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት የሚፈጸም በመሆኑ ነው።

ከዚህ ቀደም በድርጅቱ በሚፈጸም ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ምክንያት የሚያበረውን አውሮፕላን አቅጣጫ በማስቀየር ጄኔቫ ያሳረፈው ካፒቴን ሃይለምድህን አበራን በተመለከተ በወቅቱ አየር መንገዱ የሰጠው ምክንያት የአእምሮ ችግር ያለበት ነው ማለቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአንድ ወገን መለያ ሆኖ ከ20 ዓመታት በላይ መቆየቱን የሚገልጹት ሰራተኞች በተርሚናል ውስጥ የሚገኙት መደብሮች በአንድ አከባቢ ተወላጆች ቁጥጥር ስር መሆናቸውንም ለኢሳት ከውስጥ የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ላቀረቡት ክስ የአማራ ቴሌቪዥን እስከአሁን የሰጠው ምላሽ የለም።

በዚህ ጉዳይ ካፒቴን ዮሀንስ ተስፋዬን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም።