የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአመራር ለውጥ አደረገ

(ኢሳት ዲሲ– ታህሳስ 2/2011)በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአመራር ለውጥ መደረጉ ተገለጸ።

ንግድ ባንኩ በጀመረው የአሰራር ለውጥ አራት አዳዲስ ምክትልፕሬዝዳንቶች ተሹመዋል።

          ከተሾሙት አራት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ሁለቱ ከግል የንግድ ባንኮች የመጡ ናቸው ተብሏል።

ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ከመንግስት የፋይናንስ ተቋማት የመጡ መሆናቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነባር የአመራር አባላት ከተነሱ በኋላ የሃላፊነት ክፍተት ተፈጥሮ ቆይቷል።

በተለይም የአራት ዘርፎች ሃላፊዎች ከቦታቸው ከተነሱ በኋላ በምትካቸው ምደባ አልተደረገም።

ከ8 ከፍተኛ የባንክ ሃላፊዎች 6ቱ መለቀቃቸው ነው የሚነገረው።

ሃላፊዎቹ የስራ መልቀቂያ ያቀረቡት አዲሱ የኢትዮጳያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ባጫ ጊና የወሰዱትን የማሻሻያ ርምጃ ባለመቀበል ነው ተብሏል።

አዲሱ የባንኩ ፕሬዝዳንት በተቋሙ ውስጥ ረጅም አመት ያገለገሉ ዳይሬክተሮችን ከስራ ማባረራቸው ለ6ቱ ከፍተኛ አመራሮች መልቀቅ ዋነኛው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም የሚሉም አሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አስተዳደር ዋና ሃላፊ የነበሩት አቶ አባይ መሃሪ ተቋሙን የለቀቁት በገዛ ፈቃዳቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በባንኩ ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉት አቶ አባይ መሃሪ ለተቋሙ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ታዛቢዎች ይመሰክራሉ።

እሳቸው እንደሚሉትም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስራ ሲጀምሩ ተቋሙ 65 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት ነበረው።

አሁን እሳቸው ስራ ሲለቁ ግን ባንኩ የ5 መቶ 65 ቢሊየን ብር ንብረት ባለቤት ሆኗል።

ተቀማጭ ገንዘቡ ደግሞ ግማሽ ትሪሊየን ብር ደርሷል።

ለ76 ዓመታት አገልግሎት የሰጠውን ንግድ ባንክ ለመምራት ብቁና ከፍተኛ የስራ ልምድ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል።

እናም ከፍተኛ ልምድና በርካታ ዓመታት የሰሩትን ሃላፊዎች ማባረር ተገቢ አይደለም ተብሏል።

በአዲሱ ምድብ የተሾሙት አቶ ሙሉነህ አቦየ፣ ወ/ሮ እመቤት መለሰ፣ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፣ አቶ ደረጀ ኢተቻ ናቸው።

ሁሉም በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የተሾሙ ሲሆን አቶ ሙሉነህ እና አቶ ደረጀ ከአዋሽ ባንክ የመጡ ናቸው።

አቶ ኤፍሬምና ወይዘሮ እመቤት ደግሞ በመንግስት ባንክ ውስጥ የሰሩ መሆናቸው ተነግሯል።

ተሿሚዎቹ ስራቸውን የሚጀምሩት የብሔራዊ ባንክ ይሁንታ ሲሰጣቸው መሆኑን ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።