የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ኢቢኤስ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ እንዲከፍሉ ፍርድ ቤት ወሰነ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 19/2011)የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ኢቢኤስ የሚባለው የሳታላይት ጣቢያ የተሳሳተ ማስታወቂያ በማሰራጨታቸው ከ22 ሚሊየን ብር በላይ እንዲከፍሉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እና ኢቢኤስ የማስታወቂያና የብሮድካስት ህጉን በመተላለፍ ሸማቹ እንዲታለል አድርገዋል በሚል 22 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል።

የሲኖ ትራክ ተሽከርካሪን በግማሽ የቅድሚያ ክፍያ ከውጭ አስመጣላችኋለሁ በሚል በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ሰብስቦ ተሰውሯል የተባለው ዙና ትሬዲንግ ባለፈው ሐምሌ ወር ያለ አግባብ የሰበሰበውን 58 ሚሊዮን ብር ለ98 ከሳሾች እንዲመልስ በፍርድ ቤት ተወስኖበታል፡፡

በጉዳዩ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ኢቢኤስና ኢቢሲ ደግሞ ሀሰተኛ ማስታወቂያ በማሰራጨታቸው ተጠያቂ ተደርገዋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ዙና ትሬዲንግ ከተወሰነበት ከ58 ሚሊዮን ብሩ 1/4ኛውንና የተለያዩ ወጭና ማካካሻዎችን ጨምሮ ኢቢኤስና ኢቢሲ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡

በቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ የተሰራጨው የዙና ትሬዲንግ ማስታወቂያ ከውጭ ያስመጣቸው ተሽከርካሪዎች እንዳሉት የሚናገርና ተሽከርካሪዎቹ ተደርድረው በምስል የሚታዩበት እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁንና ድርጅቱ አንድም መኪና ከውጭ አለማስገባቱ መረጋገጡ ነው የተነገረው።

እናም በሀሰተኛ ማስታወቂያ ህብረተሰቡ እንዲያምነውና ዙና ትሬዲንግ ያለ አግባብ 58 ሚሊዮን ብር እንዲሰበሰብ ምክንያት ሆነዋል በሚል የሚዲያ ተቋማቱ ባሰራጩት ማስታወቂያ ፍርድ ቤቱ ተጠያቂ አድርጓቸዋል፡፡

ኢቢሲና ኢቢኤስ የማስታወቂያና የብሮድካስት ህጉን በመተላለፋቸው፣ በአሳሳች ማስታወቂያ ሸማቾች እንዲታለሉ ማድረጋቸው ተረጋግጧል።

በዚሁም መሰረት ከውል ውጭ ያለን ሀላፊነት መሰረት በማድረግ በቀረበባቸው ክስ የዋናውን ተከሳሽ እዳ 1/4ኛ ወይንም ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ባልተነጣጠለ ሀላፊነት እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡

በማስታወቂያ ህጉ መሰረት ማስታወቂያ እየተሰራለት ለእይታ የሚበቃው ቁስ በህጋዊ መንገድ ስለመገዛቱና የኢትዮጵያን ደረጃ የሚያሟላ ስለመሆኑ ማረጋገጥም የማስታወቂያ ሰሪውና አሰራጭው ሀላፊነት መሆኑን ሸገር ሬዲዮ በዘገባው አመልክቷል።