የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠበትን ምክንያት ለመግለፅ ፈቃደኛ አለመሆኑን ሃሙስ ዘገበ

ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2009)

የዜና አውታሩ በርካታ የመንግስት ተቋማት ድረ-ገጾችን ለመጎብኘት ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካለት መቅረቱን በአገልግሎቱ መቋረጥ ቢቢሲ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

የእጅ ስልክን ጨምሮ መደበኛ የብሮድባንድ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ማረጋገጥ እንደቻለ የብሪታኒያው ማሰራጫ ጣቢያ ገልጿል።

ባለፈው አመት የብሄራዊ ፈተና አፈትልኮ መውጣትን ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ያወሳው የዜና ማሰራጫው በርካታ አካላት ጉዳቱ ተመሳሳይነት ሊኖረው እንደሚችል ቢገልፅም በመንግስት በኩል ማረጋገጫ አለመሰጠቱ ታውቋል።

ይሁንና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዛድግ አብርሃ የሞባይል የስልክ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጣል ሲሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አገልግሎቱ አለመኖሩን ቢገልጹም ምክንያቱን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በተያያዘ ሁኔታም የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት እስከቀጣዩ ሳምንት ቀጣይ እንደሚሆን ሮይተርስ የመንግስት ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ ሃሙስ ዘግቧል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ሞሃመድ ሰይድ የኢንተርኔት አገልግሎት በመሰጠት ላይ ካለው የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናዎች ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ ለዜና አውታሩ ገልጸዋል።

ባለፈው አመት የተፈጠረው ክስተተ እንዳይደገም ተብሎ አገልግሎቱ ተቋርጧል በማለት ቃል አቀባዩ ለሮይተርስ አስረድተዋል።

ይሁንና አገልግሎቱ መቼ እንደሚቀጥል ቃል አቀባዩ ምላሽ አለመስጠታቸውን ከዜና አውታር ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

ሃገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች የኢንተርኔት አገልግሎት ስታቋርጥ መቆየቷን ያወሳው ሮይተርስ፣ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት በድርጊቱ ተቃውሞ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አክሎ አመልክቷል።