የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ናዝራዊት አበራን ሊጎበኝ ነው

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 27/2011)አደገኛ አፅ በማዘዋወር ተጠርጥራ በቻይና እስር ላይ የምትገኘው ናዝራዊት አበራ በኢትጵያ ልዑክ በቀጣይ ማክሰኞ እንደምትጎበኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የናዝራዊት አበራን ጉዳይ በትኩረት እየተከታተለው ይገኛል።

በቻይና ጁዋንግ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላም ናዝራዊት አበራን ለሶስት ጊዜያት እንደጎበኛት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የቻይና መንግስት እስካሁን ምንም አይነት ክስ እንዳልመሰረተም ገልጸዋል።

ወጣት ናዝራዊት አብሮ አደግ ጓደኛዋ ወደ ቻይና ለጉብኝት እንዲሄዱ ያቀረበችላትን ግብዣ ከተቀበለች በኋላ ጓደኛዋ አባቷ በድንገት ማረፋቸውን በመግለጽ የቻይና ጉዞዋን መሰረዟን ትነግራታለች።

ናዝራዊትም ጉዞውን ብቻዋን ለማድረግና ጓደኛዋ አድርሽልኝ ያለቻትን የፀጉር መታጠቢያ ሻምፑ በመቀበል ወደ ቻይና ታመራለች።

ይሁን እንጅ ቻይና ስትደርስ ያልጠበቀችው ነገር ያጋጥማታል፤ አድርሽልኝ የተባለችው እቃ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ሲፈተሽ አደንዛዥ ዕፅ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት በቁጥጥር ስር ትውላለች።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም በቻይና በተጠረጠረችበት ጉዳይ በቁጥጥር ስር ውላ በማረሚያ ቤት ትገኛለች።

ወጣት ናዝራዊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና ሙያ የተመረቀች ሲሆን በጥሩ ደመወዝ በመስራት ላይ እንደነበረችም ለማወቕ ተችሏል።