የኢትዮጵያው አገዛዝ የውጭ ብድር ቁጥጥር ያድርግ ተባለ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 5/2010)

የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ብድር ቁጥጥር እንዲያደርግና የወጭ ምርቶች ተወዳዳሪነትን እንዲያሰፋ ጠየቁ።

ኢትዮጵያ ይህን ርምጃ ካልወሰደች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊገጥማት እንደሚችል ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።

የአገዛዙ ቃለ አቃባዮች ግን የዳይሬክተሯ ጉብኝት ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ተሰሚነቷ በመጨመሩና ኢኮኖሚዋ በማደጉ የተካሄደ ነው ሲሉ የተሳሳተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የገንዘብና የእህል ዋጋ ግሽበት በእጅጉ እየጨመረ በመምጣቱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቋፍ ላይ እንደሚገኝ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በተለይ ደግሞ በንግድ ሚዛን መዛባት ምክንያት ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳጋጠማት ነው የሚነገረው።

የኢሳት ምንጮች እንደሚገልጹት በኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ ያለው የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ከ7 መቶ ሚሊየን ዶላር የሚበልጥ አይደለም።

ይህም ለ3 ሳምንታት የሚበቃ ብቻ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

እናም ከውጭ እቃ የሚያስመጡ ነጋዴዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ እስከ አንድ አመት ይጠብቃሉ ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ አገዛዝም የነዳጅና የመድሃኒት መግዣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለባት መገለጹም ነው የሚታወሰው።

ይህ አሳሳቢ ችግር ባለበት ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ያመሩት የአለም አቀፍ ገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሊወገድ የሚችለው ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የወጭ ምርት ግብይት ሲኖራት ብቻ ነው ብለዋል።

መንግስት ከውጭ እየተበደረ ከፍተኛና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መጀመሩም ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት መሆኑን ነው የገለጹት።

እናም የህወሃት አገዛዝ የውጭ ብድር ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባና ተወዳዳሪ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱን እንዲያጠናክር ዋና ዳይሬክተሯ መምከራቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።

አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር እንዲሰጠውና የእዳ ስረዛ እንዲያደረግለት የሚፈልገው የህወሃት አገዛዝ ከመንግስታዊ ልማት ይልቅ ወደ ግል ይዞታዎች እንዲያተኩርም በሴትዬዋ በኩል ግፊት በርትቶበታል።

ይህም ሆኖ ግን ዳይሬክተሯ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ኢኮኖሚያችን በማደጉና አለም አቀፍ ተቀባይነታችን በመጨመሩ ነው ሲሉ የአገዛዙ ቃልአቀባዮች ገልጸዋል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በአፍሪካ ሕብረት ንግግር ለማድረግ እቅድ ተይዞላቸው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።