የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች አዲሱን አመት ከሁለቱ ሃገራት ወታደሮች ጋ አከበሩ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 1/2011) የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ አዲሱን አመት በቡሬና ዛላ አንበሳ ግንባር ከሁለቱ ሃገራት ወታደሮች ጋ አከበሩ።

የሁለቱም ሃገራት ወታደሮች በአንድነት በመቆም ላለፉት 20 አመታት የዘለቀውን ፍጥጫ አስወግደዋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ዛሬ መስከረም 1 ቀን 2011 አመተምህረት በቅድሚያ ወደ ቡሬ ግንባር፣ከዚያም ወደ ዛላ አንበሳ በማቅናት አዲሱን አመት ከሁለቱ ሃገራት ወታደሮችና በድንበር ላይ ከሚገኙ የሁለቱ ሃገራት ዜጎች ጋር አብረው አክብረዋል።

መሪዎች በበአሉ ላይ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸውም ታውቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኡስማን ሳልህንም በበአሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በስነስርአቱ ላይ ታዳሚ እንደነበሩም መረጃዎቹ አመልክተዋል።

የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት በታደሙበት በዚህ ታሪካዊ ስነስርአት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል ሰአረ መኮንንም ተሳታፊ ሆነዋል።