የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ከነውዝግቡ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 6/2010)

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ መቀጠሉ ታወቀ።

የደህንነቱ ዋና ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንዲፈርስ ጠይቀዋል።

ብአዴንና ኦህዴድ ራሳችሁን አጥሩ በሚል በሕወሃት የቀረበው ሃሳብም ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ይህ ከፍተኛ ውዝግብ ያስከተለው ስብሰባ ሸምጋዮች እንዲገቡበት የቀረበው ሃሳብም ውድቅ ተደርጓል።

ስብሰባው ረዥም ጊዜያትን እንደሚወስድም ተገምቷል።

ሆኖም ስብሰባው ሳያልቅ የማረጋጊያ መግለጫ በቀጣዮቹ ቀናት ይወጣል ተብሎም ይጠበቃል።

ማክሰኞ እለት በተጀመረው በዚህ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ በተጨማሪ ነባር አመራሮች እየተሳተፉበት ይገኛል።

ከመከላከያና ከደህንነት የተወከሉ ግለሰቦችም በስብሰባው ላይ መገኘታቸውንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ለቀጠለው አለመረጋጋት የብአዴንና የኦሕዴድ እጅ አለበት በሚል ከሕወሃት የቀረበውን ሃሳብ ሁለቱም ድርጅቶች ተቃውመውታል።

የኦህዴድ አመራሮች አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን በስብሰባው ላይ መወረፋቸው ተመልክቷል።

በአቶ ለማ መገርሳና በአቶ አባይ ጸሃዬ መካከል የነበረው አለመግባባት ከጭቅጭቅ ያለፈ እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል።

የኦህዴድ አመራሮች በሀገሪቱ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ተገቢ ውክልና የለንም በሚል ጥያቄ ማንሳታቸውም ይፋ ሆኗል።

የሐገሪቱ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ሃላፊና የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው አሰፋ አሁን ያለው የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ሀገሪቱን የመምራት አቅም ስለሌለው መፍረስ ይገባዋል በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

እኚህ የደህንነት ባለስልጣን በስብሰባው ላይ በቋሚነት ባይሳተፉም ከደህንነት መስሪያ ቤት የመጡ ሰዎች  ግን በቋሚነት እየተሳተፉ መሆኑ ታውቋል።

በውዝግብና በጭቅጭቅ የቀጠለው የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ልዩነቱ እየሰፋ መቀጠሉን ተከትሎ ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን የጨመረ ሸምጋይ ቡድን እንዲገባ የቀረበውን ሃሳብ ብአዴንና ኦህዴድ በመቃወማቸው ውድቅ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይ የበላይነት አለ በሚል ከኦህዴድና ብአዴን የተነሳውን ሃሳብ ጨምሮ ውዝግብ የፈጠረው ስብሰባ ረዥም ጊዜያትን ሊወስድ እንደሚችል ታምኗል።

ሆኖም አለመግባባቱ አደባባይ እንዳይወጣና ለመላምቶች በር ላለመክፈት በሚል የማረጋጊያ መግለጫ በቀጣዮቹ ቀናት ይወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።