የአገዛዙ ታጣቂዎች በወሰዱት ርምጃ ከ4 በላይ ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2010)

በሐረር ከተማ በሃማሬሳ የስደተኞች ጣቢያ በሰፈሩ ሰዎች ላይ የአገዛዙ ታጣቂዎች በወሰዱት ርምጃ ከ4 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

በጥቃቱ በአጋዚ ታጣቂዎች ከተገደሉት መካከል አንድ የኦሮሚያ የጸጥታ ፖሊስ እንደሚገኝበትም ታውቋል።

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች እስከ 1 ሚሊየን እንደሚጠጉ በቅርቡ የወጡ አለምአቀፍ ሪፖርቶች ይጠቅሳሉ።

ከነዚሁ ተፈናቃዮች መካከል በሐረር ከተማ አማሬሳ የስደተኞች ጣቢያ የተጠለሉ ይገኙበታል።

የካቲት 4/2010 እሁድ በአማሬሳ የተፈናቀሉ ሰዎች ችግራቸው ሳያንሳቸው በአጋዚ ወታደሮች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

ተፈናቃዮቹ የእህል እርዳታና አስፈላጊ ቁሶች እንዲሟሉላቸው ቢጠይቁም ምላሹ ጥይት ሆኖባቸዋል።

ተፈናቃዮቹ የመልሶ ማቋቋም ሂደቱ ዘግይቷል በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸው ነው የተነገረው።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አመዴ በበኩላቸው በተከሰተው ችግር አራት ሰዎች መሞታቸውንና አስራ አንድ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጀማል ይህ ሁኔታ በምን ምክንያት እንደተፈጠረ ሲያስረዱም “ከአዲስ አበባ ወደ ሶማሌ ክልል እየተጓዘ ያለ ተሳቢ መኪና እንዲፈተሽ በክልሉ ፖሊሶችና በወጣቶቹ ጥያቄ ሲቀርብ ወዲያውኑ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ የመከላከያ ኃይል በህዝቡ ላይ የተኩስ እሩምታ ከፍቷል” ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰአት በኦሮሚያ ፖሊሶች ሲጠበቅ የነበረው የስደተኞቹ መጠለያ በሀገር መከላከያ እየተጠበቀ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አህመዲን አንዳንዶቹም ሸሽተው እየወጡም እንደሆነ ገልፀዋል።

የአጋዚ ወታሮችም ተቃውሞ ባስነሱ ወጣቶች ላይ ተኩሰው ከ4 በላይ ሰዎች መግደላቸው ነው የተነገረው።

ከነዚሁ በአጋዚ ጥይት ከተገደሉት መካከል የኦሮሚያ ፖሊስ እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል።

በአማሬሳ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት 10 ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል።

የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ዘገባዎች አመልክተዋል።

በመጠለያ ጣቢያው ከ4ሺ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ።

በዚሁ የአማሬሳ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አካባቢ ዛሬም የተኩስ ድምጽ መኖሩን መረጃዎች አመልክተዋል።