የአዲስ አበባ ወጣቶች ከጦላይ ማሰልጠኛ ሊወጡ ነው።

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 30/2011)ከአዲስ አበባ ከተማ የታፈሱትና ወደ ጦላይና ሌሎች ማሰልጠኛዎች የተወሰዱት ወጣቶች ስልጠናቸውን ጨርሰው በቅርቡ እንደሚወጡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወጣቶቹ የተያዙት ፖሊስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩና ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

አንድም የታሰረ ወጣት የለም ያሉት ኮሚሽነሩ ወጣቶቹ የተያዙት እንዲታሰሩ ሳይሆን ከህገወጥ ተግባር እንዲወጡና ስለህግ የበላይነት ስልጠና እዲያገኙ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የአዲስ አበባ ወጣቶች የተያዙት ፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወ፣ መሳሪያ ለመንጠቅና በተለያዩ ወንጀሎች ላይ በመሞከራቸው ነው።

እሳቸው እንደሚሉት ከሆነም አንድም የታሰረ የአዲስ አበባ ወጣት የለም።ለስልጠና የተወሰደ እንጂ።

ኮሚሽነሩ ወጣቶቹ በፖሊስ የተያዙት መሳሪያ የያዘ ፖሊስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ነው ብለዋል።

ወጣቶቹ የተያዙት በፖሊስ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ በማን ትዕዛዝ ፖሊስ ወጣቶቹን አፈሰ ለሚለው ግን ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም።

እንደ እሳቸው አባባል ከሆነ እነዚህ ወጣቶች ህግና ስርአትን ስለማያውቁና በህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ ነው።

ስለ ወጣቶቹ በተለያየ ወቅት የሚወጡት መረጃዎች የተለያዩ አይደሉም ያሉት ኮሚሽነሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃውን ዘግይቶ ያወጣው እስኪጣራ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ወጣትን አደገኛ ቦዘኔ ብዬ አላውቅም ያሉት ዘይኑ ጀማል ይህን የተናገረ ካለም ወንጀለኛ ነው ለፍርድ መቅረብ አለበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።