የአዲስ አበባ አበባ ቀላል ባቡር በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ሳቢያ ተስተጓጎለ

ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2009)

የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር አገልግሎት በኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት መቆራረጥ ምክንያት ስራው መስተጓጎሉን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት አስታወቀ።

የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ችግር የማይፈታ ከሆነ ድርጅቱ ተጠባባቂ የሃይል ምንጭ የሆነው ጄኔረተር ለመግዛት እቅድ መኖሩን የህዝብ ግንኙነት ሃላፌ አቶ አወቀ ሙሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። የከተማዋ ቀላል የአዲስ ባቡር አገልግሎት ከቻይና መንግስት በተገኘ 475 ዶላር ሚሊዮን ብድር ተገንብቶ ከአንድ አመት በፊት አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል።

ይሁንና ፕሮጄክቱ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ አሁን ማጋጠሙ የጀመረው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር በባቡር አገልግሎት ላይ ስጋት ማሳደሩን የተለያዩ አካላት ገልጸዋል።

የባቡር አገልግሎት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠመው የኤሌክትሪክ መቋረጥ የሚከሰተው ከብሄራዊ የኤሌክትሪክ ቋጥ በሚፈጠር ችግር መሆኑን የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ አወቀ አክለው አስረድተዋል።

በኤሌክትሪክ  ሃይል መቆራረጡ እንዲሁም አሽከርካሪዎች በባቡር ሃዲድ ላይ በሚያደርሱት ጉዳት እንዲሁም ለአገልግሎት የሚሰጡ የባቡር ቁጥሮች ማነስ የሚፈልገው አገልግሎት እንዳይሰጥ ማድረጉን ሃላፊው አክለው ገልጸዋል።

በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጡ፣ አሽከርካሪዎች በባቡር ሃዲዱ ላይ በሚያደርሱት ጉዳት፣ እንዲሁም ለአገልግሎት የሚሰጡ የባቡር ቁጥሮች ማነስ የሚፈለገው አገልግሎት እንዳይሰጥ ማድረጉን ሃላፊው አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አበባ ካህሳይ በባቡር አገልግሎት የሚያጋጥሙ የኤሌክትሪክ መቋረጥ በሃይል ማሰራጫ ጣቢያዎች በሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮች ነው ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል። ይሁንና መስሪያ ቤታቸው ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሰራ እንደሆነ የገለጹት ነገር የለም።

በቻይናው የምድር ባቡር ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ግንባታው የተከናወነው የከተማዋ ቀላል የባቡር መስመር ፕሮጄክት የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር አልቀረፈም የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት እንደነበር ይታወሳል።

የባቡር መስመሩ ከነባር የተሽከርካሪ መስመሮች ጋር የተገናኘ እና ለእግረኞች በቂ መተላለፊያ የሌለው በመሆኑ ለተገልጋዮቹ አመቺ አለመሆኑን ተጠቃሚዎች ይገልጻሉ። በዚሁ የባቡር አገልግሎት ዙሪያ በቅርቡ ዘገባን ያቀረበው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ታክሲ አገልግሎት ፊታቸውን እያዞሩ መሆኑን ዘግቧል።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑትና ድርጅቱን ለአስር አመት ያህል ጊዜ ያገለገሉት ዶ/ር ጌታቸው በትሩ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቁ ይታወሳል።

ዶ/ር ጌታቸው ሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ በምትካቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ በሻህ መሾማቸውን ሰሞኑን መዘገቡ ይታወሳል።