የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የአርበኞች ግንቦት 7 መሪዎችን ተቀበለ

የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የአርበኞች ግንቦት 7 መሪዎችን ተቀበለ
( ኢሳት ዜና ጳግሜን 05 ቀን 2010 ዓ/ም ) የከተማው ህዝብ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌንና ጨምሮ ሌሎችንም የንቅናቄው አመራሮችና አባላትን ለመቀበል ከጠዋት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ሰታዲየም በመሄድ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎአል። ህዝቡ ኮከብ የሌለበትን ሰንደቃላማ በመያዝ በጭፈራ፣ በዝማሬና የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ደስታውን ሲገልጽ ውሎአል።
ዝግጀቱን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ሃለፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ ያዩት ነገር ከጠበቁት በላይ እንደነበር ገልጸዋል።
ህዝቡ በዚህ ደረጃ ስሜቱን ሲገልጽ ለደርጅቱ አመራሮች ሸክም አይሆንባችሁም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ኤፍሬም፣ ችግሩ ከባድ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጋራ በመሆን እንፈታዋለን ብለዋል።
የአዘጋጅ ኮሚቴው አባል የሆነው ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ የዝግጅት ሂደቱ አድካሚ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ያለምንም የጸጥታ ችግር በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን፣ ለዝግጀቱ መሳካት የተለያዩ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን በማመስገን ገልጿል።
ከ10 ዓመት በሁዋላ ወደ አገሩ የተመለሰው የኢሳት ባልደረባ ደረጃ ሃብተወልድ ስለ ህዝቡ ስሜት፣ በእለቱ ስለተላለፉ መልክዕክቶች እንዲሁም ወደ አገሩ ሲመለስ ምን እንደተሰማው ጥያቄ አቅርበንለት የህዝቡ ስሜት በእጅጉ እንዳስገረመው ገልጿል