የአዲስ አበባን ጎዳናዎችና አደባባዮች ቀለም መቀባት ስህተት ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 3/2011) ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪ በሚደረገው አቀባበል የአዲስ አበባን ጎዳናዎችና አደባባዮች ቀለም መቀባት ስህተት ነው ሲል የአቀባበል ኮሚቴው ገለጸ።

የኦነግ መሪ የአቀባበል ኮሚቴ ባሰራጨው መግለጫ የተሰቀሉት የድርጅቱ አርማዎችም ቢሆኑ ከአቀባበሉ በኋላ እንደሚነሱ አስታውቋል።

ቄሮዎች ግጭትን ከሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡም የአቀባበል ኮሚቴው ጥሪ አድርጓል።

በሌላ በኩል ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሚደረገው የአቀባበል ስነ ስርዓት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄና ትብብር እንዲያደርግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መልዕክት አስተላልፏል።

ከባንዲራ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ ሰሞኑን  የተፈጠሩት ግጭቶች ተቀባይነት አይኖራቸውም ብሏል የኦሮሚያ ክልል መንግስት።

በአዲስ አበባ በአንዳንድ አከባቢዎች ከትላንት ጀምሮ መለስተኛ ግጭቶች መኖራቸውን መረጃዎች ያመልክታሉ።

ሰንደቅ ዓላማ የትግል አርማን መነሻ ያደረገው ግጭት በዛሬው ዕለትም በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። ተሽከርካሪዎች ተሰባብረዋል።

የጸጥታ አስከባሪዎች በአስለቃሽ ጢስ ተጠቅመው ግጭቱን ለማስቆም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ቅዳሜ አዲስ አበባ የሚገቡትን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ መሪን ለመቀበል እየተደረገ ያለው ዝግጅት የግጭት መንስዔ የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የትግል አርማ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለመስቀልና አንዳንድ አደባባዮችን በቀለም ለመቀባት በቄሮች እንቅስቃሴ መደረጉን ተከትሎ ነው።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የአቀባበል ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን ስህተት ሲል ገልጾታል።

ኮሚቴው በመግለጫው መንገድ ላይ በሚገኙ ደሴቶችና አደባባዮች ላይ ቀለም መቀባቱ ተገቢ አይደለም ነው ያለው።

በየጎዳናው  የተሰቀሉት የትግል አርማዎችም የአቀባበል ስነስርዓቱ ከተፈጸመ በኋላ የሚነሱ እንደሚሆኑ ኮሚቴው ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል።

የኦነግ የአቀባበል ኮሚቴ በመግለጫው ቄሮዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፏል።

የአቀባበል ፕሮግራሙን በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን ቄሮዎች ራሳቸውን ከግጭት እንዲያርቁም የአቀባበል ኮሚቴ መልዕክት አስተላልፏል።

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኦነግን አቀባበል አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ዛሬ በሰጡት መግለጫ  ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ የሚደረገው አቀባበል ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ አሰፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቋል።

መስከረም 5 የፊታችን ቅዳሜ የሚደረገው አቀባበል የህዝቡን አንድነት በሚጠብቅ መልኩ እንዲሆን ማድረግ አለበት ያሉት ዶክተር ነገሪ በሰንደቅዓላማ ሳቢያ የተፈጠረው ግጭት ተቀባይነት የሌለው ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት ምክንያት ፈልገን የምንጣላበት ሳይሆን ምክንያት ፈልገን አንድነታችንን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል ዶክተር ነገሬ ሌንጮ።