የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን የተቃወሙ የኦህዴድ ተመራጮች ከፓርላማ እንዲባረሩ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13 /2010) የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴን ስብሰባ ተከትሎ ማክሰኞ በተጀመረው  የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ የአስቸኳይ ግዜ  አዋጁን የተቃወሙ የኦህዴድ ተመራጮች ከአባልነት እንዲሁም ከፓርላማ እንዲባረሩ ህወሓት ጠየቀ።

በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከተወሰነው ውጭ  የቀረበው ይህ አጀንዳ ተቃውሞ ገጥሞታል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አመራር አባላት በተጨማሪም በአቶ ለማ መገርሳ እና በዶ/ር አብይ አህመድ ላይ የተለያዩ ክሶች ማቅረባቸውም ተሰምቷል።

እነርሱም ጠንካራ ምላሽ ሰጥተዋል

ከየአባል ድርጅቶቹ 45 በአጠቃላይ 180 አባላት እየተሳተፉበት ባለው በዚህ የኢህአዴግ ምክር ቤ ስብሰባ  የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አመራር አባላት ሁለቱን የኦህዴድ መሪዎች አቶ ለማ መገርሳንና ዶ/ር አብይ አህመድን የስልጣን ጥመኞች  በማለት የወነጀሉ ሲሆን ፣ከኢሕአዴግ  አቋም  እና ከድርጀቱ ባህል ያፈነገጡ በሚልም ተተችተዋል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በተጨማሪም  የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን የተቃወሙት የኦህዴድ አባላት ከድርጀቱ አቋም በተቃራኒ በመቆማቸው ሊባረሩ ይገባል የሚል አጀንዳ ማቅረባቸውም ተመልክቷል ።

የኢህአዴግ አጋር የሆኑት ፓርቲዎችም የኢሕአዴግ አባል ይሁኑ የሚለውንና በስራ አስፈጻሚው ውድቅ የተደርገውን አጀንዳ ሕወሃት መልሶ ለጉባኤው አቅርቧል።

ዶ/ር አብይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያ ያለችበት ቀውስ ከኢህአዴግ አቅም በላይ ነው ዕውነታውን እንጋፈጥ ሲሉ በየተራ ማሳሰባቸውን ለኢሳት የደረሰው ዜና ያስረዳል።

በእኛ ላይ የምትሰነዝሩት ክስም ሆነ ማስፈራሪያ አያሳስበንም የሚመጣውን ለመቀበል ተዘጋጅተናል  ሲሉ ሁለቱ የኦህዴድ መሪዎች  ምላሽ መስጠታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በስብሰባው ላይ ከህወሃት እና  ከሕወሃት ደጋፊዎች የሚሰነዘረውን ውንጀላ እና ክስ በመከላከል እንዲሁም ሃገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በመገምገም እነ አቶ ለማ ለሚሰጡት አስተያያት ድጋፍ የሰጡ መኖራቸውም ታውቋል።

ከ180 የምክር ቤት አባላቱ በተለይ የብአዴን እንዲሁም የደኢህዴን አባላት እነ አቶ ለማን ደግፈው የሀገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢነትን ገልጸዋል።

ወጥ አቋም ይዘው በስብሰባው እየተካፈሉ ያሉት የሕወሓት አባላት ብቻ መሆናቸውንም የመጣው ዜና ያስረዳል።

በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ወቅት ከነበሩት 36 አባላት እነ አቶ ለማን ደግፈው  ጥቂት የብአዴን አባላት  ሲቆሙ  ሕወሓት እና ደኢህዴን ወጥ ሆነው  በአንድ ድምጽ ተሰልፈው እንደነበርም ምንጮች አስታውሰዋል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በቀጠለበትና ምርጫ ባልተካሄደበት  በአሁኑ ወቅት የሕወሃት ደጋፊ  ድረ ገጾች አቶ ደመቀ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ አቶ ሼፈራው ሽጉጤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ዛሬ ጽፈዋል። የውጭ መገናኛ ብዙሃንም ይህንን መሰረት አድርገው ዘገባ በመስራት ላይ ናቸው።