የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች በመልካም አስተዳደር እጦት እየተሰቃየን ነው አሉ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 18/2011)በአርባ ምንጭ ከተማ ያለው የመልካም አስተዳደር እጦትና ኢሰብአዊ ድርጊት እየተባባሰ መምጣቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለኢሳት እንደገለጹት እንደ ሃገር መቷል የተባለው ለውጥ አርባ ምንጭ ከተማን አላካተተም።

ትላንት ከህወሃት ጋ ሆነው ህዝብን ሲያሰቃዩ የነበሩት አመራሮች አሁንም በስልጣን ላይ መሆናቸው በከተማዋ ያለውን ችግር የከፋ አድርጎታል ይላሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ኢሳት የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የህወሃት አገዛዝ ከስልጣን ተወግዶ አዲስ የለውጥ አመራር መቷል ቢባልም የአርባምንጭ ከተማ ግን ከዚህ ለውጥ ተጠቃሚ አልሆነችም ይላሉ ነዋሪዎቿ።

ትላንት በህወሃት አገዛዝ ስልጣን ላይ የነበሩት አካላት አሁንም ከተማዋን እያስተዳደሩ ነው።

ነዋሩዎቹ እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ አመራሮች ለከተማዋ ህዝብ ስጋትን ደቅነው የነበሩ አሰራሮችን ለመመለስ በመስራት ላይ ናቸው።

አመራሩ እየሄደበት ያለውን ህገወጥ አሰራር መቃወም አይቻልም።የሚቃወም ካለ ደግሞ እጣ ፋንታው የከፋ ነው ብለዋል ነዋሪዎቹ ለኢሳት።

በግፍ የታሰሩት ሰዎች እንዳይፈቱ ደግሞ የምናጣራው ጉዳይ አለን በሚል የሚጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ዜጎችን የማሰቃያ መንገድ ሆኗል ብለዋል።

አርባምንጭ በሾክ የተከበበች ከተማ ሆናለች የሚሉት ነዋሪዎቿ እየደረሰባቸው ያለውን አስከፊ ችግር ለመንገር ቢፈልጉ እንኳን ስልጣን ላይ ካለው አካል የሚያገኝ ምላሽ የለም።

አንድ ሆኖና ተከባብሮ የኖረን ሕዝብ ለማለያየት የሚሰራው ሃይል ተው ሊባል ይገባዋል ይላሉ።

በከተማዋ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ካለው የመልካም አስተዳደርና የኢሰብአዊ ድርጊት የከተዋን ችግር አሳሳቢ አድርጎታል።

የከተናማዋ ነዋሪዎች የሚያቀርቡት ጥያቄ አንድና አንድ ብቻ ነው።የፌደራል መንግስቱ በአስቸኳይ ለችግሩ መፍትሄ ሊያነጣ ይገባል።

ኢሳት በጉዳይ ላይ ምላሽ ለማግኘት ወደ ሚመለከተው አካል ያደረገው ሙከራ ሊሳካለት አልቻለም፣ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሚሰጥ አካል ካለ ኢሳት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።