የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት እስከ 16 አመታት የሚደርስ የእስር ቅጣት ተወሰነባቸው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2010)

አራት የመከላከያ አባላትን በመግደል አስር አቁስለዋል የተባሉ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት እስከ 16 አመታት የሚደርስ የእስር ቅጣት ተወሰነባቸው።

ድርጊቱን የፈጸምነው ለትልቅ ሃገራዊ አላማ እንጂ ለግል ጥቅማችን አይደለም ሲሉም ተከሳሾቹ በችሎት ውስጥ መናገራቸው ተመልክቷል።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ የቀረቡትና የቅጣት ውሳኔ የተሰጠባቸው 8 ተከሳሾች ሰኔ 25ና ሰኔ 26/2007 በትግራይ ክልል ልዩ ሃይል እንዲሁም በሚሊሺያና በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም ጉዳት ማድረሳቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

የአርበኞች ግንበት 7ን ተልዕኮ በመቀበል ሰኔ 20/2007 ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ ሰኔ 25/2007 ከቀኑ 7 ሰአት በመከላከያ ሰራዊት አባላትና በትግራይ ክልል ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ተብሏል።

በዚህም ጥቃት ምክትል ኮማንደር ወልደሚካኤል ገብረእግዚአብሔር፣የመቶ አለቃ ሃጎስ ኪዳነማርያም እንዲሁም ሚኒሻ ካህሳይ ነጋሽን ጭንቅላት፣ደረትና ሆድ ላይ በመምታት ገድለዋል ሲል ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ላይ ዘርዝሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለት የሃምሳ አለቃና የአስር አለቃ ማዕረግ ያላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ 5 ሰዎችን ካቆሰሉ በኋላ ከአካባቢው በመሸሽ በሌላ ስፍራ በቀጣዩ ቀን ጥቃት መሰንዘራቸውን ፍርድ ቤቱ በቅጣት ውሳኔው ላይ ዘርዝሯል።

እነዚሁ ታጣቂዎች በቀጣዩ ቀን ሰኔ 26/2007 በጸገዴ ወረዳ ወርኢ ከዛ በተባለ ቦታ 5 የትግራይ ክልል ሚሊሻዎችን ማቁሰላቸውም ተመልክቷል።

ከዚያም በቀጣዮቹ ቀናት እስከ ሰኔ 28 ከመከላከያ ሰራዊት አባላትና ከትግራይ ክልል ሚሊሻዎች ጋር ውጊያ ሲያደርጉ ቆይተዋው መማረካቸውን በውሳኔው ላይ የዘረዘረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በዚህ ድርጊታቸው እስከ 16 አመታት የሚዘልቅ እስራት እንደወሰነባቸው አስታውቋል።

አቃቤ ሕግ በዚህ ዙሪያ የመሰረተውን ክስ በተመለከተ አንከላከልም ያሉት 8ቱ ተከሳሾች ዛሬ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ተከሳሾቹ የገደልነውና ያቆሰልነው ንጹሃን ሰዎችን ሳይሆን የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በመሆኑ እንዲሁም ድርጊቱን የፈጸምነው ለግል ጥቅማችን ሳይሆን ለትልቅ ሃገራዊ አላማ ነው በማለት የቅጣት ማቅለያ አቅርበዋል።

ሃገራዊ ተልዕኮ ነው የፈጸምነው ባሉት በአገኘው ካሱና ነበረ ፋንታሁን ላይ የ15 አመታት እስራት ሲፈረድ ስማቸው አምበሉ፣ባባዬ አዛናው፣አስቻለው ክፍሌ፣ደሴ ክንዴ፣ክብረት አያሌው፣ብርሃኑ ዳርጌና አወቀ መኮንን ደግሞ የ16 አመታት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ሌሎች 6 ተከሳሾች ግን እንከላከላለን በማለታቸው የክስ ሒደቱ በእነሱ ላይ ቀጥሏል።