የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አዲስ ማሳሰቢያ አወጣ

ኢሳት (ሰኔ 6 ፥ 2009)

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አዲስ ማሳሰቢያ አወጣ። ሚኒስቴሩ ማክሰኞ ባወጣው ማሳሰቢያ እንዳለው አስቸኳይ ጊዜ ከታወጀበት ከመስከረም 2009 በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ ብዛት ያላቸው ሰዎች ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጿል። 

ሚኒስትሩ በድጋሚ በድረገጹ ያወጣው የጉዞ ጥንቃቄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀጣይ ከተደረገበት እኤአ ከ ማርች 2017 ጀምሮ በአማራ ክልል በባህርዳርና በጎንደር አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አብራርቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎትን በማወኩና የስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጡ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አሜሪካውያን ጋር ግንኙነት እንዳያደርጉ ማስተጓጎሉን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ መንግስት አገልግሎት ሲያቋርጥም ለአሜሪካ እንደማያሳውቅም በድረገጹ አስፍሯል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ ዜጎች ሲታሰሩ ለአሜሪካ መንግስት እንደማያሳውቅ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብራርቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስካሁን በተግባር ላይ ነው ያለው የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ አሜሪካውያን በሰላማዊ ሰልፎችና በስብሰባ ቦታዎች ላይ እንዳይገኙ፣ ለደህንነታቸው ሲባል አካባቢያቸው ላይ ያለውን ሁኔታ መገምገም እንደሚኖርባቸው ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ ሰላማዊ ቢሆኑም እንኳን፣ ተቃውሞውን ለመበተን ሃይል እንደሚጠቀም፣ ይህም በሰልፈኞች ላይ ጥይት በመተኮስ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የአሜሪካ ዜጎችን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ሰላማዊ ሰልፎች በመንግስት ሃይሎች የሃይል እርምጃ ከገጠማቸው ወደብጥብጥ ሊገቡ እንደሚችሉም ማሳሰቢያው አክሎ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች የደህንነታቸውን ሁኔታ መከታተልና፣ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ የማምለጫ መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው ገልጿል።

ከተራዘመው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ ለመተንበይ አስቸጋሪ የሆነ የደህንነት ችግር በመኖሩ በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ተለዋጭ የግንኙነት መስመር ሊኖራቸው ይገባል ሲል ገልጿል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች የስልክ ቁጥራቸውን በኢምባሲው እንዲያስመዘግቡና በየጊዜው የሚወጡ የጉዞ ማሳሰቢያዎችን በጽሁፉ መልክ (SMS) መቀበል እንዲችሉ አሳስቧል።