የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አዛዥ ለትግራይ ህዝብ ጥሪ አቀረቡ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2011)የትግራይ ህዝብ በህወሃት መሪዎች የሚደረገውን የጦርነት ትንኮሳ እንዲያወግዝ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አዛዥ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አዛዡ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ እንደገለጹት የህወሃት የመከላከያና የደህንነት ሃላፊዎች የትግራይን ህዝብ ለአላስፈላጊ ግጭት እየቀሰቀሱት ነው፡፡

በሌብነትና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ ወንጀል በመፈጸም ትግራይ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙት የህወሃት የጦር ጄነራሎች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት የትግራይን ህዝብ ለጦርነት ለመማገድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ብለዋል ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ፡፡

የአማራ ክልል መንግስት መከላከል ላይ ያተኮረ ዝግጅት እያደረገ ነው ያሉት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ወደ ጦርነት የማያስገቡ ሰላማዊ መንገዶች ቅድሚያ ተሰጥቶባቸው እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ሆነው የተሾሙት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ የህወሃት መሪዎች ለጦርነት የሚያበቃ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀዋል ነው የሚሉት፡፡

የትግራይ የመከላከያ፤ የደህንነትና የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በተለየ ሁኔታ ወታደራዊ ስልጠና ማካሄድ የጀመሩት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ህዝባዊ ንቅናቄ ከተቀጣጠለበት ጊዜ አንስቶ መሆኑን የገለጹት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ከለውጡ በኋላ በሙሉ ሃይል ስልጠናውን ማካሄዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች ጄነራል አብርሃም ወልደማርያም፤ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ እንዲሁም ከደህንነት አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመሩት ስልጠና ባለፉት ስድስት ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ለጦርነት ዝግጁ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ከፍተኛ ወታደራዊ መሳሪያዎች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በማስቀረት ለጦርነት የተዘጋጀውን ሃይል እንዲታጠቅ መደረጉንም ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ አንስተዋል፡፡

የትግራይን ህዝብ ለጦርነት ለመማገድ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኙት የህወሃት የጦር ሰራዊትና የደህንነት መሪዎች ኢትዮጵያ በእጃቸው በነበረችበት ወቅት በመጠነ ሰፊ የሌብነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ እንደተዘፈቁ የሚጠረጠሩ ናቸው ይላሉ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፡፡

እነዚህ አመራሮች ከተጠያቂነት ለማምለጥ በሚል የትግራይን ህዝብ ወንድም ከሆነው የአማራ ህዝብ ጋር ደም ለማቃባት ቆርጠው ተነስተዋል ሲሉ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ገልጸዋል፡፡

ጥቃት ሊፈጸምብህ ነው፤ ወረራ ሊካሄድብህ ነው የሚለው ቅስቀሳም በስፋት እየተካሄደ ነው ይላሉ፡፡

የአማራ ክልላዊ መንግስት በህወሀት በኩል የሚደረገውን የጦርነት መሰል ዝግጅት አስፈላጊ ነው ብሎ አያምንም የሚሉት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ሰላማዊ መንገድን ከመከተል ውጪ አማራጭ እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና በመከላከል ላይ ያተኮረ አስፈላጊ ዝግጅት በአማራ ክልል በኩል በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ዕውነቱን የሚያውቅ በመሆኑ ለገዢዎቹ የጦርነት ድግስ ህይወቱን አይገብርም ያሉት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ይህን በመገንዘብ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ጥሪ አድርገዋል፡፡ ለቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ጓደኞቻቸው ለሆኑትና የትግራይን ህዝብ ለጦርነት እያዘጋጁት ላሉት የህወሃት የጦር መሪዎች ምክር አስተላልፈዋል፡፡