የአማራና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ሰላም ለማምጣት እንሰራለን አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2011) የአማራና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች የሁለቱ ክልል ሕዝብ ወደ ግጭት እንዳይገባ እንደሚሰሩ በሃይማኖት አባቶችና በሃገር ሽማግሌዎች ፊት ቃል ገቡ።

የአማራና የትግራይ ክልል ህዝብ አንዱ ለአንዱ ስጋት ሳይሆን አንዱ በሌላው እየኮራ ተከባብሮ የሚኖርበት ታሪክ ነበረው ሲሉ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገልጸዋል።

የአማራና የትግራይ ህዝብ በመካከላቸው ችግር የለም ችግሩ ያለው እኛ ፖለቲከኞቹ ዘንድ ነው ያሉት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የፖለቲካ ልዩነት ሰላማችንን እንዲያውከው አንፈቅድም ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ጥሪና ተማጽኖ አዲስ አበባ ላይ ተገኝተው የጋራ መግለጫ የሰጡት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ችግራቸውን በውይይት ለመፍታትም ቃል ገብተዋል።

“የአማራ ህዝብ የተለያዩ አጀንዳዎች አሉት እነዚህ አጀንዳዎቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እንጂ ከወንድሙ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንዲጋጭ አንፈልግም “ በማለት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሲገልጹ።

ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው በአማራ ላይ ምንም የምናነሳው ጥያቄ የለም ብለዋል።

የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ወገኖች ሊያበጣብጡን ነው የሚሞክሩት ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የወሰንን ጉዳይ በተመለከተ እንኳን የውስጣችንን የውጭ ሃገር መፍታት ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሁለቱ ክልል ፕሬዝዳንቶች በጋራ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የሃይማኖት አባቶቹና የሃገር ሽማግሌዎች ሁለቱን የክልል መሪዎች አመስግነዋል።

አርአያነት ያለው ተግባር ፈጽማችኋል ሲሉም አሞግሰዋል።