የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደረገ

ጥር ፪ (ሁለት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በመላው ኢትዮጵያ በነዳጅ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ንግድ ሚንስቴር አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ቤንዚን በሊትር 16 ብር ከ61 ሳንቲም የነበረው አንድ ብር ከ13 ሳንቲም ጨማሪ ተደርጎበት17 ብር ከ92 ሳንቲም እንዲሸጥ ተብሎአል። ነጭ ናፍጣ 14 ብር ከ16 ሳንቲም የነበረው አንድ ብር ከ02 ሳንቲም ጭማሪ ተደርጎበት 15 ብር ከ18 ሳንቲም ይሸጣል።  ኬሮሲን በሊትር 13 ብር ከ65 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 13 ብር ከ57 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 12 ብር ከ93 ሳንቲም ሲሸጥ የአውሮፕላን ነዳጅ ደግሞ በሊትር 15 ብር ከ49 ሳንቲም ለተጠቃሚው መቅረቡን ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ይህ የዋጋ ማስተካከያ የተደረገው ባለፉት ሶስት ወራት በዓለም ላይ የነዳጅ ምርቶች ላይ ጭማሪ መከሰቱን ምክንያት በማድረግ ነው ሲል መስሪያቤቱ ገልጿል። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው አሁን የሚታየውን የዋጋ ንረት የበለጠ ይጨምረዋል የሚል ስጋት ማሳደሩን ዘጋቢያችን ገልጿል።