የቻግኒ ከተማ ደማቅ የድጋፍ ሰልፍ አደረገች

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 29/2010) በምዕራብ ጎጃም የቻግኒ ከተማ ደማቅ የድጋፍ ሰልፍ አደረገች።

የድጋፍ ሰልፉ በዳውሮና በሌሎችም የደቡብ ክልል አካባቢዎች መካሄዱ ታውቋል።

አርባምንጭ ለነገው የድጋፍ ሰልፍ የሚደረገውን ዝግጅት የከተማዋ አመራር እያደናቀፈ መሆኑ ተገለጿል።

በውጭ ሀገራትም በኢትዮጵያ የሚታየውን የለውጥ ጅምር በመደገፍ ሰልፎች መካሄዳቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በጄኔቫ ስዊዘርላንድ፣ በስቶክሆልም ስዊዲን፣ በካናዳ ቶሮንቶ ኢትዮጵያውያን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ቻግኒ ዛሬ የህወሀት አገዛዝ የተወገዘበትን ትዕይንት ነበር ያስተናገደችው።

የኮከብ ምልክት በሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ የደመቀው ትዕይንትን በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በመሳተፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፋቸውንም አሳይተዋል።

የዘረኝነት በሽታ ትክክለኛ ዶክተር ሲሉ ነው የቻግኒ ነዋሪዎች ለዶክተር አብይ ድጋፋቸውን የገለጹት።

ቻግኒዎች በከተማዋ ስር የሰደደውን የሙስና ችግር በመንቀስ የቀን ጅቦች አደብ እንዲገዙ ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላለፉበት ሰልፍ እንደነበረ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

እንደ ባህርዳሮች ረዥሙን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የታዩት የቻግኒ ነዋሪዎች ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ መልዕክቶችንና ጭፈራዎችን በማሰማት ሰልፉን አድምቀውት እንደነበረ በቪዲዮ ተደግፎ የወጣው መረጃ ያመለክታል።

ሚሊሺያ ወደ እርሻ፣ ደላላና ማዘጋጃ ይለያዩና ሌሎች መፈክሮችንም ማሰማታቸው ታውቋል።

ረዥሙን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ በመውጣት ሰሞኑን የቦንጋ ነዋሪዎችም ያደረጉት የድጋፍ ሰልፍ ልዩ ድምቀት እንደነበረው ከስፍራው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በቦንጋው ሰልፍ ታዋቂው ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉን ጨምሮ የተለያዩ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን የተወደሱበት ነበር።

በተመሳሳይ ዜናም የዳውሮ ዞን ነዋሪዎች በተርጫ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ማድረጋቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ ሰንደቅ ባሸበረቀው የተርጫው ሰልፍ ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህምድ የለውጥ ጅምር ድጋፉን አሳይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በነገው ዕለት በአርባምንጭ ለሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ ነዋሪው ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑም ታውቋል።

ረዥም የተባለ ሰንድቅ ዓላማ ያዘጋጁት የአርባምንጭ ነዋሪዎች በነገው ዕለት ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ፣ ለተጀመረው የለውጥ ሂደት ድጋፉን የሚገልጽ ሰልፍ እንደሚያደርጉ በመግለጽ ላይ ናቸው።

የከተማው አንዳንድ አመራሮች እንቅፋት በመፍጠር ሰልፉን ሊያጨናግፉት እየሞከሩ በመሆኑ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ነዋሪዎቹ አስጠንቅቀዋል።

በጎጃም እንጅባራና ኮሰበር፣ በሰሜን ጎንደር ዳባት የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የድጋፍ ሰልፍ እንደተዘጋጀም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮዮጵያውያንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ጅምር ድጋፋቸውን የገለጹባቸውን ሰልፎች በማድረግ ላይ ሲሆኑ በትላንትናው ዕለት በስዊዲን ስቶክሆልም፣ በካናዳ ቶሮንቶ ደማቅ ትዕይንተ ህዝብ መካሄዱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በስዊዘርላንድ ጄኔቫም እንዲሁ ኢትዮጵያውያን ለውጡን በመደገፍ ሰልፍ አድርገዋል።

በየከተሞቹ በሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎች ላይ ኤርትራውያን በመገኘት አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆኑም ታውቋል።

በተያያዘ ዜና በሰኔ 16ቱ የአዲስ አበባ የድጋፍ ሰልፍ በደረሰው የቦምብ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አጋርነትን ለማሳየት በሚል ከቦረና ዞን የተላከ ድጋፍ መድረሱ ተገለጸ።

የቦረና ዞን አስተዳደር፣ አባገዳዎችና ቄሮዎች በጋራ የላኳቸው ከ160 በላይ ፍየሎች በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች መሰጠቱንም ለማወቅ ተችሏል።