የትሕዴን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ ናቸው

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 28/2011)ከ2ሺህ በላይ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትሕዴን/ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

ወታደሮቹን ጭነው ከሚጓዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች አንዱ በደረሰበት የመገልበጥ አደጋ ሶስት ወታደሮች መሞታቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ መንግስትና በትህዴን መካከል በቅርቡ አስመራ ላይ ውይይት መደረጉን ተከትሎ በዛሬው እለት በዛላምበሳ ለገቡት ወታደሮች አቀባበል እንደሚደረግ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በ1993 ዓመተምህረት የተመሰረተው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ትህዴን በትጥቅ ትግል 19ዓመታትን ቆይቷል።

የመጀመሪያ መሪውን በግድያ ሁለተኛውን በኩብለላ ያጣው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ትህዴን የህወሀትን አገዛዝ በመሳሪያ ትግል ለማስወገድ የተቋቋመ እንደሆነ ይገልጻል።

ህወሀት ለህዝብ የገባውን ቃል በማጠፍ ጭቋኝ ስርዓት ሆኗል በሚል ጫካ የገቡት የትህዴን ታጋዮች በኢትዮጵያ እኩልነት እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የሚያስችል ትግል እያካሄደ እንደነበረ ንቅናቄው ካሰራጫቸው ጽሁፎች መረዳት ይቻላል።

ሁለተኛው መሪው ሞላ አስገዶም ከህወሀት ደህንነቶች ጋር በመሆን የተወሰኑ ወታደሮችን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መኮብለላቸው የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ትጥቅ ያነሱ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት መግባት የጀመሩ ሲሆን ትህዴንም ሀምሌ 7 2010 ዓመተምህረት በይፋ የትጥቅ ትግል ማቆሙን አስታውቆ ነበር።

የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ ጀነራል አደም ኢብራሂም ወደ ኤርትራ በማምራት ከትህዴን አመራሮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሊቀመንበሩ አቶ መኮንን ተስፋዬ የሚመራው የትህዴን አመራር ቡድን ወደ ሀገር ቤት ኢትዮጵያ ገብቷል።

በወቅቱ የትህዴንን አመራሮች በአዲስ አበባ የተቀበሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

በኤርትራ ብረት አንስተው ይታገሉ ከነበሩ የተለያዩ ቡድኖች መሀል በሰራዊት ቁጥር ቀዳሚ የሆነው የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ትህዴን ከዛሬ ጀምሮ ሰራዊቱን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት መጀመሩን የደረሰን ዜና ያመለክታል።

በዛላምበሳ በኩል ከ2ሺህ በላይ የትህዴን ሰራዊት መግባት የጀመረ ሲሆን በሆደት ቀሪ የሰራዊቱ ክፍል ጠቅልሎ እንደሚገባም ለማወቅ ተችሏል።

ለሰራዊቱ የአቀባበል ፕሮግራም የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት አለመቻሉን ጠቅሰዋል።

በተያያዘ ዜና ከኤርትራ ወደ ሀገር ቤት በማምራት ላይ ባለው የትህዴን ሰራዊት በአንደኛው የማጓጓዥ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ አደጋ ሶስት ወታደሮች መሞታቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

በኤርትራ የድንበር ከተማ ሰገነይቲ በምትባል አከባቢ በደረሰው አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ 20 ወታደሮች ጉዳት ደርሶባቸው በኤርትራ ደቀማሀሪ ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።