የቴፒና አካባቢው ነዋሪዎች ድብደባና እንግልት እየበዛብን ነው አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 21/2011)የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ድብደባና እንግልት እየፈጸመብን ነው ሲሉ የቴፒና አካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።

በአካባቢው የሸካና ማጃንግ ብሔረሰብ አባላት የማንነት ጥያቄያችን ይፈታ በሚል ጥያቄ በማንሳታቸው ግጭት ተፈጥሯል።

በዞኑና በአካባቢው ያሉ አመራሮች ወጣቶችን ከጀርባችሁ ሌላ ሃይል አለ በማለት በልዩ ሃይል እያስደበደቧቸው መሆናቸው ታውቋል።

በግጭቱ አንድ ሚስጥሩ ሲሳይ የተባለ ወጣት በጥይት መቁሰሉም ታውቋል።

በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ሁሉም የንግድ በደብሮች ዝግ ናቸው።

በቴፒ ከተማ በአየር ሜዳ፣መናሃሪያ በከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ ሰፈሮች እንዲሁም ቆጮ ተራ በሚባለው አካባቢ በርካታ ወጣቶች በደቡብ ክልል ልዩ ሃይል እየተደበድቡ መሆናቸው ነው የተነገረው።

ምክንያቱ ደግሞ የሸካና የማጃንግ ብሔረሰብ አባላት የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ነው ተብሏል።

በዞኑ ያሉ አመራሮች የደቡብ ክልል ልዩ ሃይልና የፌደራል ፖሊስ ጠርተው ሕዝቡን እያንገላቱ መሆናቸውም ተነግሯል።

አመራሮቹ ከጥያቄው በስተጀርባ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አሉበት በሚል ወጣቶችን እያስደበደቡ ነው ተብሏል።

መነሻው ደግሞ ሚስጥሩ ሲሳይ የተባለ ወጣት በጥይት በመቁሰሉ እንደሆነም ነው የተነገረው በዚህ ሰበብ ግጭቱ ተባብሶ ሌሎች ሁለት ወጣቶች መቁሰላቸውም ተገልጿል።

ከነዚህ መካከል አንዱ የ14 አመት ታዳጊ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ጅማ በሚባለው ሰፈር በርካታ ወጣቶች እየተደበደቡ ናቸው ተብሏል።

እናም መንግስት በታጠቁ ሃይሎች ከመደብደብ ያድነን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሸካ ዞን ቴፒ ሕዝቡ በስጋት ውስጥ መሆኑ ይነገራል።

በአካባቢው ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ከዚህ ቀደም በርካታ ሰዎች ሲሞቱ የተፈናቀሉ እንደነበሩም መዘገባችን አይዘነጋም።