የተለያዩ የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ኢሳትን “በጸረ-ኦሮሞነት” ከሰሱ

የተለያዩ የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ኢሳትን “በጸረ-ኦሮሞነት” ከሰሱ
( ኢሳት ዜና መስከረም 15 ቀን 2011 ዓ/ም ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ፣ የተባበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፣ የኦሮምያ ነጻነት አንድነት ግንባር እና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በጋራ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ወይም ኢሳት ተብሎ የሚጠራው ጸረ-ኦሮሞ የሚዲያ ተቋም በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሃሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከጀመረ የሰነባበተ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞን ህዝብና ከኦሮሞ ህዝብ አብራክ የተገኘውን ቄሮ እንደ ጭራቅ በመሳል የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደበት ይገኛል ብሎአል።
ድርጅቶቹ በመግለጫቸው በተለይም የቡራዩን ክስተት መንስዔና ሂደት አቅጣጫ በማንሳት የዘር ጭፍጨፋ የተፈጸመ በማስመሰል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ህዝብ ከህዝብ እንዲጋጭ ከማድረግ ባሻገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ለማግኘት እየተጠቀሙበት ነው ብለዋል። ከውጭና ከውስጥ እጅና ጓንት በመሆን ሃገርን የምታመሱ የመገናኛ ብዙሃን በህግም በታሪክም ፊት ተጠያቂ መሆናችሁን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አስገንዝበዋል።
መግለጫውን የሰጡት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ዲማ ነገኦና ሌሎችን ፖለቲከኞች በጸረ-ኦሮሞነት ከከሰሱት ከኢሳት ሚዲያ ጋር ተደጋጋሚ ቃለምልልሶችን ማድረጋቸው ይታወቃል።
ድርጅቶቹ በመግለጫቸው በቡራዩ በተፈጸመው ድርጊት ጀርባ ጸረ ኦሮሞ አቋም ያለው የተደራጀ የፖለቲካ ቡድን ስለመኖሩ መረጃዎች ተገኝተዋል ያሉ ሲሆን፣ ድርጊቱን የፈጸሙና በበላኢነት የሚመሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። ድርጅቶቹ የ ግለሰቦችንና የቡድኖችን ስም በመግለጫቸው አልጠቀሱም።
መግለጫው “ የኦሮሞ ህዝብ በፊንፊኔ ላይ ያለው የመብት ጥያቄ በኦሮምያ ላይ ካለው የሃገር ባለቤትነት የመብት ጥያቄ ተነጥሎ አይታይም” ያሉ ሲሆን፣ “አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከተማይቱ የሁሉም ብሄረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ አንጻር ህዝቦች የግልም ሆነ የቡድን መብታቸው ያለ አንዳች መሸራረፍ ሊከብርላቸው እንደሚገባ አያጠራጥረም “ ብሏል።
ድርጅቶቹ “ በነጻ ምርጫ ተወዳድረው ማሸነፍ እንደማይችሉ ከወዲሁ የተገነዘቡ የፖለቲካ ቡድኖች በሃሰት የብር ኖቶች ዜጎችን አታለው የሃይማኖትና የብሄር ግጭት በማስነሳት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሃገሪቱን ማስተዳደር የተሳነው በማስመሰል የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ በማድረግ የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት እየተሯሯጡ” በመሆናቸው፣ አሁን ያሉት ተቋማት በትክክል እንዲሰሩ ተደርጎ፣ በነጻ ተዓማኒና በቂ ፉክክር በተደረገበት ህዝባዊ ምርጫ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር ብቻ የምንደግፍ መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል።
በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን ፌደራሊዝም ለማፍረስ የሚደረገውን ሙከራ ድርጅቶቹ በህልውናቸው ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው እንደሚወስዱት አስታውቀዋል።