የብሪታኒያ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ የሚፈልጉ የሃገሪቱ ዜጎች አማራጭ የመገናኛ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አሳሰበ

ኢሳት (ግንቦት 24 ፥ 2009)

መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጡን ተከትሎ የብሪታኒያ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ የሚፈልጉ የሃገሪቱ ዜጎች አማራጭ የመገናኛ መንገዶችን እንዲጠቀሙ አሳሰበ።

ከማክሰኞ ጀምሮ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን የገለጸው የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ኢትዮጵያ የመጓዝ እቅድ ያላቸው ዜጎች የሞባይልና የመደበኛ ስልኮችን በአማራጭነት እንዲጠቀሙ ባሰራጨው የጉዞ ጥንቃቄ ማሳሰቢያው አመልክቷል።

እስራትን ጨምሮ የድብደባና ሌሎች አደጋዎች የሚያጋጥማቸው ብሪታኒያውያን ለአገልግሎቱ ሲባል በተከፈተ የስልክ ቁጥር ሪፖርት እንዲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪውን አቅርቧል።

ቤተሰቦቻቸው ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙባቸውና ስጋት ያደረባቸው የሃገሪቱ ዜጎችም ለተመሳሳይ አገልግሎት በብሪታኒያ ጥቅም ላይ የዋለ የስልክ ቁጥር መጠቀም እንዲችሉ በዚሁ የጉዞ ማሳሰቢያ ተገልጿል።

የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከወራት በፊት በጎንደርና በባህርዳር ከተሞች የደረሱ የቦንብ ፍንዳታዎችን ተከትሎ የሃገሪቱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ ዕርምጃን እንዲያደርጉ ሲያሳስብ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎት በምን ምክንያት እንደተቋረጠ በይፋ የሰጠው ምክንያት የሌለ ሲሆን፣ የተለያዩ አካላት አገልግሎት ረቡዕ መስጠት የጀመረውን የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በህገወጥ መንገድ እንዳይሰራጭ ለማድረግ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የአገልግሎቱን መቋረጥ ተከትሎ በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የሚኖሩ ተጠቃሚዎች ለችግር መዳረጋቸውን እየገለጹ ይገኛል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ሆነ የትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ረቡዕ የጀመረው የብሄራዊ ፈተና እስከ ቀጣዩ ሳምንት ቀጣይ እንደሚሆን ለመረዳት ተችሏል።

በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን አስመልክቶ ሰፊ ዘገባዎችን እያቀረቡ ይገኛል።

ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት የብሄራዊ ፈተና በማህበራዊ ድረገጾች መሰራጨቱን ተከትሎ ፈተናው በድጋሚ እንዲሰጥ ተደርጎ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ይታወሳል።

በወቅቱ የመንግስት ባለስልጣናት አገልግሎቱ ለብሄራዊ ፈተናው ሲባል መቋረጡን ይፋ አድርገዋል።

ባለፈው አመት በሃገሪቱ ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ መቆየቱን ዘጋርዲያን ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባው አውስቷል።