የባህርዳር እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎችን በመለየት የእስር ርምጃ ሊወሰድ ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 2/2010)

በአማራ ክልል የባህርዳር እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎችን በመለየት የእስር ርምጃ ሊወሰድ መሆኑን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገለጹ።

የእስር ርምጃውን ለመውሰድ ወሳኔ ላይ የተደረሰው በከተማዋ ያለውን ተቃውሞ የሚያንቀሳቅሱት የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎች ናቸው የሚል የደሕንነት መረጃ በመቅረቡ ነው።

በጉዳዩ ላይ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት፥ ከመከላከያ መረጃ ክፍል፥ ከአድማ ብተና እና ከመደበኛ ፖሊስ የተውጣጡ ሃላፊዎች በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክክር አድርገዋል።

የአካባቢው የመረጃ ምንጮች እንደጠቆሙት የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎች እየተመረጡ እንዲታሰሩ የተወሰነው በጨዋታ ሜዳዎች በሰላማዊ መንገድ አገዛዙን የሚቃወሙ ሁኔታዎች አሳይተዋል በሚል ነው።

በተለይ ባለፈው እሁድ ጥር 27/2010 የባህር ዳር ከነማ ከመድህን እግር ኳስ ክለብ ጋር ሲጫወት ወጣቶች የሕወሃትን ዘረኛ አገዛዝ በማውገዝ መቃወማቸው ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል።

ከጨዋታው በኋላም አብዛኛው የባህርዳር ከተማ ወጣቶች ከሜዳ እንደወጡ እጃቸውን በማጣመር ተቃውሞ አሰምተዋል።

በዚሁም የአድማ በታኝ ፖሊስ ርምጃ ባለመውሰዱ ተጠያቂ ነው የሚል ክስ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል።

የክልሉ አድማ በታኝ ዋና አዛዥ ኮማንደር መለስአለም ትዕዛዝ ስላልደረሰኝ ርምጃ አልወሰድኩም ሲል መልስ መስጠቱም ነው የተገለጸው።

ይህንኑ ተከትሎም የደህንነት ሃላፊዎች የባህርዳሩን ተቃውሞ የሚመሩት የከተማዋ እግር ኳስ ደጋፊዎች ናቸው ማለቱ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሳይቀር ትኩረት እንዲደረግ ትዕዛዝ ተላልፏል።

የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሕወሃት በኩል በመጣባቸው ጫና የባህርዳር ከነማ ደጋፊዎችን እስከማነጋገር ደርሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ደጋፊዎቹን በመለየት የማሰር ርምጃ ሊወሰድባቸው መሆኑም ተነግሯል።

በርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ ተሳትፎ ቢሮ ሃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ በተመራው ስብሰባ የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት፣ የመከላከያ መረጃ ክፍል አድማ በታኝና መደበኛ ፖሊስ በእስር ርምጃ አወሳሰዱ ላይ ምክክር ማድረጋቸው ታውቋል።

በዚሁም መሰረት ወጣቶችን በጅምላ ማፈስ አስቸጋሪ በመሆኑ አፈሳው ከባህርዳር ቀበሌ 04ና 05 ወጣቶች በጥንቃቄ እንዲጀመር መወሰኑ ነው የተነገረው።

ወጣቶችን የማሰሩ ዘመቻም የባህርዳር ከተማ ፖሊስ የምርመራ ክፍል ሃላፊ ኮሚሽነር ጥበበ ሃይሌ እንዲመራው የተወሰነ መሆኑን ከአካባቢው የደረሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።