የቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር ወደ 10 ዝቅ ተደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 27/2011) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን 20 ቋሚ ኮሚቴዎችና አንድ ልዩ ኮሚቴ በመሰብሰብ ወደ 10 ዝቅ ማድረጉን አስታወቀ።
ለቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ከተጠቆሙት አባላት ውስጥ ፓርላማው የሁለቱን ውድቅ ማድረጉም ተመልክቷል።


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ ሁለት ቋሚ ኮሚቴዎችን እንዲመሩ የተጠቆሙትን አቶ ሞቱማ መቃሳንና አቶ አማኑኤል አብርሃምን ውድቅ ያደረገበት ምክንያት ግን አልተገለጸም።
የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትና በቅርቡ ከዚህ ሃላፊነታቸው የተነሱት አቶ ሞቱማ መቃሳ የምክር ቤቱን የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲመሩ በእጩነት የቀረቡ ቢሆንም ፓርላማው ሳይቀበለው ቀርቷል።
በተመሳሳይ የሕግ፣ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮችን እንዲመሩ በእጩነት የቀረቡትን አቶ አማኑኤል አብርሃምንም ምክር ቤቱ ውድቅ ማድረጉም ተመልክቷል።