የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት አባላት ስማችንና ክብራችን ይመለስልን አሉ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 18/2011) የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት አባላት አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው መንግስት የተቀማነውን ስማችንንና ክብራችንን ያስመልስልን ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ።

የሰራዊት አባላቱ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት በአርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ አማካኝነት መሆኑም ታውቋል።

አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ 800 ያህል ለሚሆኑ የሰራዊቱ አባላት የምስጋናና የአክብሮት የምሳ ግብዣ ማድረጉም ተመልክቷል።

ከ22 አመታት በኋላ ወደ ሃገሩ የተመለሰው አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከተለያዩ የህብረትሰብ ክፍሎች ጋር በመገናነት ምስጋናና ክብር በመስጠት ግብዣ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ዛሬ ላይ ደግሞ የምስጋናና የአክብሮት የምሳ ግብዣ ስነስርአቱን ለቀድሞ የጦር ሰራዊት አባላት አድርጓል።

800 የሚሆኑ የሰራዊቱ አባላት ተገኝተዋል በተባለበት በዚህ ስነስርአት ላይ የቀድሞ የምድር ጦር፣የባህር ሃይል፣የአየር ሃይል፣የአየር ወለድና ሌሎች የሰራዊቱ አባላት ተገኝተዋል።

የጦር ሰራዊት አባላቱ በስነስርአቱ ላይ ለሃገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት አንስተዋል።

በተለይም እኛ የሃገራችንን ድንበር ለማስጠበቅ መስዋዕት ከፍለን እንጂ ሃገር ለመውረር አልዘመትንም ሲሉ ተናግረዋል የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባላት።

ከተለያየ ክፍል የወጡ የሰራዊቱ አባላትም መፈክሮቻቸውን ያስተላለፉና ለሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ያላቸውን አክብሮት በመግለጽ በቀጣይም የተነጠቅነውን ስማችንና ክብራችንን አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት እንዲያስመልስልን ሲሉ ጥያቄያቸውን በአርቲስት ታማኝ በየነ በኩል አቅርበዋል።

በስነስርአቱ ላይ የተገኙት የጦር ጉዳተኞችም የያዝነውንም ተነጥቀናል፣ጥያቄያችን ሊሰማና መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ በታማኝ በየነ በኩል ለመንግስት አስተላልፈዋል።

በስነስርአቱ ላይ የቀድሞ ሰራዊት አባላት በክፍሎቻቸው አማካኝነት ለአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ስጦታ አበርክተውለታል።