የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የጦር አካዳሚ መኮንኖች ማህበር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 21/2011)የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የጦር አካዳሚ መኮንኖች ማህበር ለግሎባል አልያንስ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

ለአክቲቪስት ታማኝ በየነም የምስጋና እና የሽልማት ስነ-ስርዓት አካሂዷል።

አክቲቪስት ታማኝ በየነ ለቀድሞ ሰራዊት አባላት ላሳየው ወገናዊነትና ተቆርቋሪነት ሽልማት ማበርከቱን የማህበሩ መሪዎች ገልጸዋል።

እሁድ ጥር 19/2011 በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደውና የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር አካዳሚ መኮንኖች ማህበር ባዘጋጀው ስነ-ስርዓት ቀደምት የአካዳሚው መኮንኖች የተገኙ ሲሆን የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮለኔል ጎሹ ወልዴም በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የቀዳማዊ ሃይለስላሴ የጦር መኮንኖች አካዳሚ ማህበር ባዘጋጀው ስነ-ስርዓት ማህበሩ ለአክቲቪስት ታማኝ በየነ ያዘጋጀውን ሽልማት የሐረር ጦር አካዳሚ ምሩቅና የማህበሩ አባል ሻለቃ ሃይለማርያም አባይ አበርክተዋል።

በተለይ ለቀድሞው ሰራዊት ባሳየው ወገናዊነትና ተቆርቋሪነት ማህበሩ ሽልማቱን እንዳበረከተለትም በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር መኮንኖች አካዳሚ ማህበር ከዚህም በተጨማሪ በታማኝ ሰብሳቢነት የሚመራው ግሎባል አልያንስ የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማመስገን ለግሎባል አሊያንስ ማጠናከሪያ የ5 ሺህ ዶላር ስጦታም አበክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በውጭ ሃገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባቀረቡት ጥሪ መሰረትም የአካዳሚው ማህበር አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ምላሽ እንዲሰጡም በስነ-ስርዓቱ ላይ ጥሪ ቀርቧል።

አክቲቪስት ታማኝ በየነም ከቀዳማዊ ሃይለስላሴ ጦር አካዳሚ ማህበር አባላት የተሰጠውን ሽልማት በከፍተኛ አክብሮት መቀበሉን ገልጿል።